ኢሳይያስ 10:20-27

ኢሳይያስ 10:20-27 NASV

በዚያ ቀን ከእስራኤል ዘር የተረፉት፣ ከያዕቆብም ቤት የዳኑት፣ ከእንግዲህ ወዲህ በመታቸው ላይ አይታመኑም፤ ነገር ግን በእስራኤል ቅዱስ በእግዚአብሔር ላይ፣ በእውነት ይታመናሉ። የተረፉት ይመለሳሉ፣ ከያዕቆብ ቤት የተረፉት ወደ ኀያሉ አምላክ ይመለሳሉ። እስራኤል ሆይ፤ ሕዝብህ በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ቢሆንም፣ ትሩፉ ብቻ ይመለሳል። ጽድቅ የሰፈነበት ጥፋት ታውጇል። የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ የወሰነውን ጥፋት በምድር ሁሉ ላይ ይፈጽማልና። ስለዚህ ጌታ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በጽዮን የምትኖሩ ሕዝቤ ሆይ፤ ግብጽ እንዳደረገብህ ሁሉ በትር ያነሡብህን፣ በሽመል የደበደቡህን አሦራውያንን አትፍራቸው። በአንተ ላይ ያመጣሁትን ቅጣት በጥቂት ጊዜ ውስጥ አቆማለሁ፤ በእነርሱም ላይ መቅሠፍቴን አመጣለሁ።” የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድያምን በሔሬብ ዐለት አካባቢ እንደ መታ፣ በጅራፍ ይገርፋቸዋል፤ በግብጽ እንዳደረገውም ሁሉ፣ በትሩን በውሆች ላይ ያነሣል። በዚያ ቀን ሸክማቸው ከትከሻህ፣ ቀንበራቸውም ከዐንገትህ ላይ ይነሣል፤ ከውፍረትህም የተነሣ ቀንበሩ ይሰበራል።