ሐጌ 2

2
ቃል የተገባው የአዲሱ ቤት ክብር
1በሰባተኛው ወር፣ በሃያ አንደኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል በነቢዩ በሐጌ በኩል እንዲህ ሲል መጣ፤ 2“ለይሁዳ ገዥ ለሰላትያል ልጅ ለዘሩባቤል፣ ለሊቀ ካህናቱ ለኢዮሴዴቅ#2፥2 በዕብራይስጡ ዬሆሳዛዴክ የሚል ሲሆን የኢዩሴዴቅ ሌላ አጠራር ነው፤ በቍጥር 4 ላይ አለ። ልጅ ለኢያሱ፣ ከምርኮ ለተረፈውም ሕዝብ እንዲህ ብለህ ተናገር፤ እንዲህም ብለህ ጠይቃቸው፤ 3‘ይህን ቤት በቀድሞ ክብሩ ሳለ ያየ ከመካከላችሁ ማን አለ? አሁንስ ምን መስሎ ይታያችኋል? ይህ በፊታችሁ ምንም እንዳይደለ የሚቈጠር አይደለምን?’ 4የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘አሁን ግን ዘሩባቤል ሆይ፤ በርታ፤ የሊቀ ካህናቱ የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ ሆይ፤ በርታ፤ እናንተም የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ በርቱ’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘እኔ ከእናንተ ጋራ ነኝና ሥሩ’ ይላል ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር5‘ከግብጽ በወጣችሁ ጊዜ የገባሁላችሁ ቃል ይህ ነው፤ መንፈሴም በመካከላችሁ ይሆናልና አትፍሩ።’
6“የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በቅርቡ፣ አንድ ጊዜ እንደ ገና ሰማያትንና ምድርን፣ ባሕሩንና የብሱን አናውጣለሁ። 7ሕዝቦችን ሁሉ አናውጣለሁ፤ የሕዝቦችም ሀብት ሁሉ ወደዚህ ይመጣል፤ ይህንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ’ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር8‘ብሩ የእኔ ነው፤ ወርቁም የእኔ ነው’ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር9‘የዚህ የአሁኑ ቤት ክብር ከቀድሞው ቤት ክብር ይበልጣል’ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ‘በዚህም ቦታ ሰላምን እሰጣለሁ’ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።”
ተግሣጽና በረከት
10ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣ በዘጠነኛው ወር፣ በሃያ አራተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል በነቢዩ በሐጌ በኩል እንዲህ ሲል መጣ፤ 11“የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሕጉ ምን እንደሚል ካህናቱን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፤ 12አንድ ሰው የተቀደሰውን ሥጋ በልብሱ ዕጥፋት ቢይዝ፣ ያም ዕጥፋት እንጀራ ወይም ወጥ፣ የወይን ጠጅ ወይም ዘይት ወይም ሌላ ምግብ ቢነካ የተቀደሰ ይሆናልን?’ ”
ካህናቱም፣ “የተቀደሰ አይሆንም” ብለው መለሱ።
13ሐጌም፣ “ሬሳ በመንካቱ የረከሰ ሰው፣ ከእነዚህ አንዱን ቢነካ፣ የተነካው ነገር ይረክሳልን?” ሲል ጠየቀ።
ካህናቱም፣ “አዎን፣ ይረክሳል” ሲሉ መለሱ።
14ከዚያም ሐጌ እንዲህ አለ፤ “ ‘ይህ ሕዝብና ይህ ወገንም በፊቴ እንደዚሁ ነው’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘የእጃቸው ሥራና የሚያቀርቡት ሁሉ የረከሰ ነው።’
15“ ‘እንግዲህ ከዛሬ ጀምራችሁ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ከመነባበሩ በፊት የነበረውን ሁኔታ አስተውሉ።#2፥15 ወይም ላለፉት ቀናት እንደ ማለት ነው። 16አንድ ሰው ሃያ መስፈሪያ ወደሚሆን የእህል ክምር በመጣ ጊዜ ዐሥር ብቻ አገኘ፤ ዐምሳ ማድጋ የወይን ጠጅ ለመቅዳት ወደ መጭመቂያው በሄደ ጊዜ ሃያ ብቻ አገኘ። 17የእጃችሁን ሥራ ሁሉ በዋግ፣ በአረማሞና በበረዶ መታሁት፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም’ ይላል እግዚአብሔር18‘ከዚህ ቀን ጀምሮ፣ ይኸውም ከዘጠነኛው ወር ሃያ አራተኛ ቀን ጀምሮ፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠረት እስከ ተጣለበት ቀን ድረስ ያለውን ዘመን አስተውሉ፤ ልብ ብላችሁም አስቡ፤ 19በጐተራ የቀረ ዘር አሁንም ይገኛልን? የወይኑና የበለሱ ዛፍ፣ የሮማኑና የወይራው ዛፍ እስካሁን አላፈሩም።
“ ‘ከዚህ ቀን ጀምሮ እባርካችኋለሁ።’ ”
እግዚአብሔር ለዘሩባቤል የሰጠው ተስፋ
20በወሩ ሃያ አራተኛ ቀን የእግዚአብሔር ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ ሐጌ መጣ፤ 21“ለይሁዳ ገዥ ለዘሩባቤል ሰማያትንና ምድርን እንደማናውጥ ንገረው፤ 22የመንግሥታትን ዙፋን እገለብጣለሁ፤ የባዕዳንን መንግሥታት ኀይል አጠፋለሁ፤ ሠረገሎችንና ሠረገለኞችን እገለብጣለሁ፤ ፈረሶችና ጋላቢዎቻቸውም በገዛ ወንድሞቻቸው ሰይፍ ይወድቃሉ።
23“የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በዚያ ቀን ባሪያዬ የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤል ሆይ፤ እኔ እወስድሃለሁ’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘እንደ ማተሚያ ቀለበቴ አደርግሃለሁ፤ እኔ መርጬሃለሁና’ ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።”

Currently Selected:

ሐጌ 2: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ