እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “አንባቢው እንዲፈጥን፣ ራእዩን ግልጽ አድርገህ በጽላት ላይ ጻፍ። ራእዩ የተወሰነለትን ጊዜ ይጠብቃልና፤ ስለ መጨረሻውም ይናገራል፤ እርሱም አይዋሽም፤ የሚዘገይ ቢመስልም ጠብቀው፤ በርግጥ ይመጣል፤ ከቶም አይዘገይም። “እነሆ፤ እርሱ ታብዮአል፤ ምኞቱ ቀና አይደለም፤ ጻድቅ ግን በእምነቱ ይኖራል። በርግጥ የወይን ጠጅ አታልሎታል፤ ትዕቢተኛ ነው፤ ከቶ አያርፍም፤ እንደ መቃብር ስስታም ነው፣ እንደ ሞት ከቶ አይጠግብም፤ ሕዝቦችን ለራሱ ይሰበስባል፤ ሰዎችንም ሁሉ ማርኮ ይወስዳል። “ታዲያ በእንደዚህ ዐይነቱ ሰው ላይ በማፌዝና በመዘበት እንዲህ እያሉ ሁሉም አይሣለቁበትምን? “ ‘የራሱ ያልሆነውን ለራሱ ለሚያከማች፣ ራሱን በዐመፅ ባለጠጋ ለሚያደርግ ወዮለት! ይህ እስከ መቼ ይቀጥላል?’ ባለዕዳ ያደረግሃቸው ድንገት አይነሡብህምን? ነቅተውስ አያስደነግጡህምን? በእጃቸውም ትወድቃለህ። አንተ ብዙ ሕዝብ ስለ ዘረፍህ፣ የተረፉት ሕዝቦች ይዘርፉሃል፤ የሰው ደም አፍስሰሃልና፤ አገሮችንና ከተሞችን፣ በውስጣቸው የሚኖሩትን ሁሉ አጥፍተሃል። “በተጭበረበረ ትርፍ መኖሪያውን ለሚገነባ፣ ከጠላት እጅ ለማምለጥ፣ ቤቱን በከፍታ ላይ ለሚሠራ ወዮለት! የብዙ ሰዎች ነፍስ እንዲጠፋ አሢረሃል፤ በገዛ ቤትህ ላይ ውርደትን፣ በራስህም ላይ ጥፋትን አምጥተሃል። ድንጋይ ከቅጥሩ ውስጥ ይጮኻል፤ ከዕንጨት የተሠሩ ተሸካሚዎችም ይመልሱለታል። “ከተማን ደም በማፍሰስ ለሚሠራ፣ በወንጀልም ለሚመሠርታት ወዮለት! ሰዎች፣ ለእሳት ማገዶ እንዲሆን እንዲለፉ፣ ሕዝቦችም በከንቱ እንዲደክሙ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ወስኖ የለምን? ውሃ ባሕርን እንደሚሸፍን ሁሉ፣ ምድርም የእግዚአብሔርን ክብር በማወቅ ትሞላለችና። “ኀፍረተ ሥጋቸውን ለማየት፣ ባልንጀሮቹን ለሚያጠጣ፣ እስኪሰክሩም ድረስ ለሚቀዳላቸው ወዮለት! በክብር ፈንታ ዕፍረት ትሞላለህ፤ አሁን ደግሞ ተራው የአንተ ነውና ጠጣ፤ ኀፍረተ ሥጋህም ይገለጥ፤ በእግዚአብሔር ቀኝ እጅ ያለው ጽዋ ይመለስብሃል፤ ክብርህንም ውርደት ይሸፍነዋል። በሊባኖስ ላይ የሠራኸው ግፍ ያጥለቀልቅሃል፤ እንስሳቱን ማጥፋትህም ያስደነግጥሃል፤ የሰው ደም አፍስሰሃልና፤ አገሮችንና ከተሞችን በውስጣቸው የሚኖሩትንም ሁሉ አጥፍተሃልና። “የሰው እጅ የቀረጸው ጣዖት፣ ሐሰትንም የሚናገር ምስል ምን ፋይዳ አለው? ሠሪው በገዛ እጁ ሥራ ይታመናልና፣ መናገር የማይችሉ ጣዖታትን ይሠራልና። ዕንጨቱን፣ ‘ንቃ!’ ሕይወት የሌለውንም ድንጋይ፣ ‘ተነሣ!’ ለሚል ወዮለት! በውኑ ማስተማር ይችላልን? እነሆ፤ በወርቅና በብር ተለብጧል፤ እስትንፋስም የለውም።” እግዚአብሔር ግን በተቀደሰ መቅደሱ አለ፤ ምድር ሁሉ በፊቱ ጸጥ ትበል።
ዕንባቆም 2 ያንብቡ
ያዳምጡ ዕንባቆም 2
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዕንባቆም 2:2-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች