ዮሴፍ በአባቱ ፊት ተደፍቶ አለቀሰ፤ ሳመውም። ከዚያም ዮሴፍ የአባቱ የእስራኤል ሬሳ እንዳይፈርስ ባለመድኀኒት የሆኑ አገልጋዮቹ በመድኀኒት እንዲቀቡት አዘዘ። ባለመድኀኒቶቹም እንዳይፈርስ ሬሳውን በመድኀኒት ቀቡት። ሬሳው እንዳይፈርስ መድኀኒት መቀባቱ በአገሩ ልማድ መሠረት አርባ ቀን ወሰደባቸው፤ ግብጻውያንም ሰባ ቀን አለቀሱለት። የሐዘኑ ጊዜ እንዳበቃ ዮሴፍ የፈርዖንን ቤተ ሰዎች እንዲህ አላቸው፤ “በፊታችሁ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ፣ ለፈርዖን እንዲህ ብላችሁ ንገሩልኝ፤ ‘የምሞትበት ጊዜ ስለ ተቃረበ፣ በከነዓን ምድር ራሴ ቈፍሬ በአዘጋጀሁት መቃብር እንድትቀብረኝ’ ሲል አባቴ አስምሎኛል፤ ስለዚህ ወደዚያ ሄጄ አባቴን ልቅበር፤ ከዚያም እመለሳለሁ።” ፈርዖንም፣ “በአስማለህ መሠረት ሄደህ አባትህን ቅበር” አለው። ከዚያም ዮሴፍ አባቱን ለመቅበር ወጣ፤ የፈርዖን ሹማምት በሙሉ፣ የቤተ መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች እንዲሁም የግብጽ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች ሁሉ ተከተሉት። እንደዚሁም የዮሴፍ ቤተ ሰዎች፣ ወንድሞቹና ሌሎችም የአባቱ ቤተ ሰዎች በሙሉ ዐብረውት ሄዱ። በጌሤም የቀሩት ሕፃናት ልጆቻቸው፣ የበግ፣ የፍየልና የከብት መንጋዎቻቸው ብቻ ነበሩ። እንዲሁም ሠረገሎችና ፈረሰኞች ዐብረውት ወጡ፤ አጀቡም እጅግ ብዙ ነበረ። እነርሱም በዮርዳኖስ ማዶ ካለው አጣድ ከተባለው ዐውድማ ሲደርሱ፣ ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ ምርር ብለው አለቀሱ፤ ዮሴፍም በዚያ ለአባቱ ሰባት ቀን ልቅሶ ተቀመጠ። በዚያ የሚኖሩ ከነዓናውያን በአጣድ ዐውድማ የተደረገውን ልቅሶ ባዩ ጊዜ፣ “ይህ ለግብጻውያን መራራ ልቅሷቸው ነው” አሉ። በዮርዳኖስ አጠገብ ያለው የዚያ ቦታ ስም አቤል ምጽራይም ተብሎ መጠራቱም ከዚሁ የተነሣ ነበር።
ዘፍጥረት 50 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 50
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 50:1-11
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች