ዘፍጥረት 44:1-34

ዘፍጥረት 44:1-34 NASV

ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ለቤቱ አዛዥ እንዲህ ሲል መመሪያ ሰጠው፤ “የሰዎቹ ስልቻ የሚይዘውን ያህል እህል፣ እንዲሁም ብር በየስልቻቸው አፍ ክተተው። ከዚያም የብር ዋንጫዬን በታናሹ ወንድማቸው ስልቻ አፍ ከእህሉ ዋጋ ጋራ ጨምረው።” አዛዡም ዮሴፍ እንዳለው አደረገ። ጎሕ ሲቀድ ሰዎቹ ከነአህዮቻቸው ተሸኙ። ከከተማው ምንም ያህል ርቀው ሳይሄዱ፣ ዮሴፍ የቤቱን አዛዥ እንዲህ አለው፤ “እነዚያን ሰዎች ቶሎ ድረስባቸውና፣ ‘ለበጎ ነገር ስለ ምን ክፉ መለሳችሁ? ይህ ጌታዬ የሚጠጣበት፣ የተሰወረ ነገርም የሚያውቅበት ጽዋ አይደለምን? የፈጸማችሁት ድርጊት ክፉ ነው’ ” በላቸው። የቤቱ አዛዥም እንደ ደረሰባቸው፣ ልክ እንደ ተባለው ተናገራቸው። እነርሱ ግን እንዲህ አሉት፤ “ጌታችን እንዲህ ያለ ነገር ለምን ይናገራል? እኛ አገልጋዮችህ እንዲህ ያለውን ነገር አናደርገውም። ከዚህ ቀደምም በየስልቾቻችን አፍ የተገኘውን ብር ከከነዓን እንኳ መልሰን አምጥተናል፤ ታዲያ አሁን ብር ወይም ወርቅ ከጌታህ ቤት እንዴት እንሰርቃለን? የጠፋው ዕቃ ከአገልጋዮችህ የተገኘበት ይሙት፤ የቀረነው የጌታችን ባሮች እንሁን።” እርሱም “መልካም ነው፤ እንዳላችሁት ይሁን፤ ጽዋው የተገኘበት ሰው ባሪያዬ ይሆናል፤ የቀራችሁት ግን ከበደሉ ነጻ ትሆናላችሁ” አላቸው። እያንዳንዱ ሰው ጭነቱን ወዲያውኑ አራግፎ ስልቻውን ፈታ። ከዚያም አዛዡ ፍተሻውን ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ቀጠለ። በመጨረሻም፣ ጽዋው በብንያም ስልቻ ውስጥ ተገኘ። በዚህ ጊዜ ልብሳቸውን በሐዘን ቀደዱ፤ ሁሉም ስልቾቻቸውን በየአህዮቻቸው ጭነው ወደ ከተማዪቱ ተመለሱ። ይሁዳና ወንድሞቹ ወደ ዮሴፍ ቤት ሲገቡ፣ እርሱ ገና ከቤቱ አልወጣም ነበር። እነርሱም ከፊቱ መሬት ላይ ተደፉ። ዮሴፍም፣ “ለምን እንዲህ ያለ ነገር አደረጋችሁ? እንደ እኔ ያለ ሰው ስውር ነገርን የሚያውቅበት ልዩ ጥበብ እንዳለው አታውቁምን?” ሲል ጠየቃቸው። ይሁዳም፣ “ከእንግዲህ ለጌታችን ምን ማለት እንችላለን? ምንስ እንመልሳለን? እንዲህ ካለው በደል ንጹሕ መሆናችንን ማስረዳትስ እንዴት ይቻለናል? እግዚአብሔር የእኛን የአገልጋዮችህን በደል ገልጧል፤ ከእንግዲህ ጽዋው የተገኘበት ብቻ ሳይሆን ሁላችንም ባሮችህ ነን” አለ። ዮሴፍም፣ “ይህንስ ፈጽሞ አላደርገውም፤ ባሪያዬ የሚሆነው ጽዋው የተገኘበት ሰው ብቻ ነው፤ የቀራችሁት በሰላም ወደ አባታችሁ ተመለሱ” አላቸው። ይሁዳም ወደ ዮሴፍ ቀረብ ብሎ፣ “ጌታዬ ሆይ፤ እኔ አገልጋይህ አንዲት ቃል ብቻ ልናገር፤ አንተም የፈርዖንን ያህል የተከበርህ ስለ ሆንህ፣ እባክህን እኔን አገልጋይህን አትቈጣኝ። ጌታዬ፣ ‘አባት ወይም ወንድም አላችሁ?’ ብሎ አገልጋዮቹን ጠይቆ ነበር። እኛም፣ ‘አዎን፣ ሽማግሌ አባት አለን፤ አባታችንም በስተርጅና የወለደው ትንሽ ልጅ አለው፤ ወንድምየው ሞቷል፤ ከአንድ እናት ከተወለዱት ልጆች መካከል የተረፈው እርሱ ብቻ ነው፤ አባቱም በጣም ይወድደዋል’ ብለንህ ነበር። “ከዚያም አንተ አገልጋዮችህን፣ ‘እንዳየው ወደ እኔ አምጡት’ አልኸን። እኛም ለጌታዬ ‘ልጁ ከአባቱ ሊለይ አይችልም፤ ከተለየው ደግሞ አባትየው ይሞታል’ አልንህ። አንተ ግን እኛን አገልጋዮችህን፣ ‘ታናሽ ወንድማችሁ ዐብሯችሁ ወደዚህ ካልመጣ ዳግመኛ ፊቴን አታዩም’ አልኸን። እኛም ወደ አገልጋይህ ወደ አባቴ በተመለስን ጊዜ፣ አንተ ጌታዬ ያልኸንን ነገር ነው። “ከዚያም አባታችን ‘እስኪ ተመልሳችሁ ጥቂት እህል ሸምቱልን’ ሲለን፤ ‘መሄድ አንችልም፤ መሄድ የምንችለው ታናሽ ወንድማችን ዐብሮን ሲሄድ ብቻ ነው። ታናሽ ወንድማችንን ይዘን ካልሄድን በቀር፣ የሰውየውን ፊት ማየት አንችልም’ አልነው። “አገልጋይህ አባቴም እንዲህ አለን፤ ‘ሚስቴ ሁለት ወንዶች ልጆች እንደ ወለደችልኝ ታውቃላችሁ፤ አንዱ በወጣበት በመቅረቱ፣ “በርግጥ የአውሬ እራት ሆኗል” አልሁ፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ይኸው የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል። አሁን ደግሞ ይህን ልጅ ወስዳችሁ አንዳች ጕዳት ቢደርስበት ሽበቴን በመሪር ሐዘን ወደ መቃብር ታወርዱታላችሁ።’ “እንግዲህ አሁን ልጁን ሳንይዝ ወደ አገልጋይህ ወደ አባቴ ብመለስ፣ ሕይወቱ ከልጁ ሕይወት ጋራ በጥብቅ የተሳሰረ ስለ ሆነ፣ የልጁን ከእኛ ጋራ አለመኖር ሲያይ አባቴ ይሞታል። ከዚህም የተነሣ እኛ አገልጋዮችህ የአባታችንን ሽበት በመሪር ሐዘን ወደ መቃብር እናወርደዋለን። እኔ አገልጋይህ፣ ‘ልጅህን መልሼ ሳላመጣ ብቀር፣ ለዘላለም በደለኛ አድርገህ ቍጠረኝ’ በማለት፣ ስለ ልጁ ደኅንነት በአባቴ ፊት ራሴን ዋስ አድርጌአለሁ። “ስለዚህ አሁን፣ አገልጋይህ በልጁ ፈንታ የአንተ የጌታዬ ባሪያ ሆኜ እዚሁ ልቅር፤ ልጁ ግን ከወንድሞቹ ጋራ ይመለስ። ልጁን ሳልይዝ እንዴት ተመልሼ ወደ አባቴ እሄዳለሁ? ፈጽሞ አላደርገውም፤ እባክህ በአባቴ ላይ የሚደርሰውን መከራ እንዳይ አታድርገኝ።”

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}