በስልቻዎቻቸው እህል እንዲሞሉላቸው፣ ብሩንም በእያንዳንዱ ሰው ስልቻ ውስጥ መልሰው እንዲያስቀምጡና ለጕዟቸው ስንቅ እንዲያሲዟቸው ዮሴፍ ትእዛዝ ሰጠ። ይህም ከተደረገላቸው በኋላ፣ እህላቸውን በአህዮቻቸው ጭነው ጕዟቸውን ቀጠሉ። በመንገድም ለዐዳር ሰፍረው ሳሉ፣ ከእነርሱ አንዱ ከያዘው እህል ላይ ለአህያው ለመስጠት ስልቻውን ሲፈታ፣ በስልቻው አፍ ላይ ብሩን አገኘ። እርሱም ወንድሞቹን፣ “ኧረ ብሬ ተመልሶልኛል፤ ይኸው ስልቻዬ ውስጥ አገኘሁት” አላቸው። ሁሉም ልባቸው በድንጋጤ ተሞልቶ እየተንቀጠቀጡ በመተያየት፣ “እግዚአብሔር ምን ሊያመጣብን ይሆን?” አሉ። በከነዓን ምድር ወዳለው ወደ አባታቸው ወደ ያዕቆብ ከደረሱ በኋላ፣ ያጋጠማቸውን ሁሉ እንዲህ ብለው ነገሩት፤ “የአገሩ ጌታ የሆነው ሰው ምድሪቱን እንደምንሰልል ቈጥሮን በቍጣ ተናገረን። እኛ ግን እንዲህ አልነው፤ ‘እኛ የታመንን ሰዎች እንጂ ሰላዮች አይደለንም። እኛ የአንድ አባት ልጆች የሆንን፣ ዐሥራ ሁለት ወንድማማቾች ነን፤ አንዱ የለም፤ ታናሽ ወንድማችን ግን ከአባታችን ጋራ በከነዓን ይገኛል።’ “ከዚህ በኋላ የአገሩ ጌታ የሆነው ሰው እንዲህ አለን፤ ‘ታማኝ ሰዎች መሆናችሁን የማውቀው በዚህ ነው፤ ከእናንተ መካከል አንዱን ወንድማችሁን እዚህ እኔ ዘንድ ትታችሁ የተቀራችሁት ለተራቡት ቤተ ሰቦቻችሁ እህል ይዛችሁላቸው ሂዱ። ነገር ግን ታናሽ ወንድማችሁን ወደ እኔ አምጡት። በዚያም ጊዜ ታማኝ ሰዎች እንጂ ሰላዮች አለመሆናችሁን ዐውቃለሁ፤ ወንድማችሁንም መልሼ እሰጣችኋለሁ፤ እናንተም በምድሪቱ እንደ ልብ ለመዘዋወር ትችላላችሁ።’ ” እህሉንም ሲዘረግፉ በየስልቾቻቸው ውስጥ ብራቸው እንደ ተቋጠረ ተገኘ፤ የእያንዳንዳቸውን የተቋጠረ ብር ሲያዩም፣ እነርሱም ሆኑ አባታቸው ደነገጡ። አባታቸው ያዕቆብም፣ “ያለ ልጅ እኮ አስቀራችሁኝ፤ ዮሴፍ የለም፤ ስምዖንም የለም፤ አሁን ደግሞ ብንያምን ልትወስዱ ትፈልጋላችሁ፤ ኧረ ምን ጕድ ነው የመጣብኝ!” አላቸው። በዚህ ጊዜ ሮቤል አባቱን፣ “መልሼ ባላመጣው፣ ሁለቱን ወንዶች ልጆቼን ግደላቸው፤ ኀላፊነቱን ለእኔ ተውልኝ፤ እኔው መልሼ አመጣዋለሁ” አለው። ያዕቆብም፣ “ልጄ ዐብሯችሁ ወደዚያ አይወርድም፤ ወንድሙ እንደሆን ሞቷል፤ የቀረው እርሱ ብቻ ነው። ይዛችሁት ስትሄዱ በመንገድ ላይ አደጋ ቢደርስበት፣ ሽበቴን በመሪር ሐዘን ወደ መቃብር ታወርዱታላችሁ” አላቸው።
ዘፍጥረት 42 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 42
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 42:25-38
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች