ያዕቆብ በግብጽ እህል መኖሩን ሲሰማ፣ ልጆቹን እንዲህ አላቸው፤ “ለምን እርስ በርስ ትተያያላችሁ? በግብጽ እህል መኖሩን ሰምቻለሁ፤ ስለዚህ ከመሞት መሰንበት ይሻላልና ወደዚያው ወርዳችሁ እህል ሸምቱልን” አላቸው። ከዚያም ዐሥሩ የዮሴፍ ወንድሞች እህል ለመሸመት ወደ ግብጽ ወረዱ። ነገር ግን ያዕቆብ የዮሴፍን ወንድም ብንያምን፣ ክፉ ነገር ይደርስበታል በሚል ፍርሀት ከወንድሞቹ ጋራ አልላከውም። ራቡ በከነዓንም በመበርታቱ፣ እህል ለመሸመት ወደ ግብጽ ከሄዱት ሰዎች መካከል የእስራኤል ልጆችም ነበሩ። በዚህ ጊዜ ዮሴፍ የምድሪቱ ገዥ ነበር፤ ለአገሩ ሰዎች ሁሉ እህል የሚሸጥላቸው እርሱ ነበር። የዮሴፍ ወንድሞችም እንደ ደረሱ፣ ከፊቱ ቀርበው ወደ ምድር ለጥ ብለው እጅ ነሡት። ዮሴፍም ወንድሞቹን ገና ሲያያቸው ወዲያውኑ ዐወቃቸው፤ ነገር ግን እንደማያውቃቸው ሆኖ፣ “ከየት የመጣችሁ ናችሁ?” ብሎ በቍጣ ቃል ተናገራቸው። እነርሱም፣ “እህል ለመሸመት ከከነዓን ምድር የመጣን ነን” ብለው መለሱለት። ዮሴፍ ወንድሞቹን ቢያውቃቸውም እንኳ እነርሱ ግን አላወቁትም። በዚህ ጊዜ ዮሴፍ ስለ ወንድሞቹ ያየው ሕልም ትዝ አለውና፣ “ሰላዮች ናችሁ፤ የመጣችሁት አገራችን በየትኛው በኩል ለጥቃት የተጋለጠች መሆኗን ለመሰለል ነው” አላቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “ጌታችን ሆይ፤ እንዲህስ አይደለም፤ አገልጋዮችህ የመጣነው እህል ለመሸመት ነው፤ ሁላችንም የአንድ አባት ልጆች ነን፤ አገልጋዮችህ የታመንን ሰዎች እንጂ ሰላዮች አይደለንም።” እርሱም መልሶ፣ “አይደለም፤ የመጣችሁት አገራችን በየት በኩል ለጥቃት የተጋለጠች መሆኗን ለመሰለል ነው” አላቸው። እነርሱ ግን መልሰው፣ “እኛ አገልጋዮችህ በከነዓን አገር ከሚኖር ከአንድ ሰው የተወለድን ዐሥራ ሁለት ወንድማማቾች ነን። ትንሹ ወንድማችን አባታችን ዘንድ ሲሆን፣ አንዱ ግን የለም” አሉት። ዮሴፍም እንዲህ አላቸው፤ “ነገርኋችሁ እኮ፤ ሰላዮች ናችሁ! ታናሽ ወንድማችሁ እዚህ እስካልመጣ ድረስ ከዚህ ንቅንቅ እንደማትሉ በፈርዖን ስም እምላለሁ፤ ማንነታችሁ የሚረጋገጠውም በዚህ ነው። በሉ፣ ከእናንተ አንዱን ላኩና ወንድማችሁን ይዞ ይመለስ፤ የቀራችሁት ግን የተናገራችሁት ቃል እውነትነቱ እስኪረጋገጥ ድረስ እስር ቤት ትቈያላችሁ። እንደ ተናገራችሁት ካልሆነ ግን፣ በፈርዖን ስም እምላለሁ፤ ሁላችሁም ሰላዮች ናችሁ” አላቸው። ሁሉንም ሦስት ቀን በእስር አቈያቸው። በሦስተኛውም ቀን ዮሴፍ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ እግዚአብሔርን ስለምፈራ እንዲህ በማድረግ ሕይወታችሁን አትርፉ። ታማኝ ሰዎች ከሆናችሁ፣ ከመካከላችሁ አንዱ እዚህ እስር ቤት ሲቈይ፣ የቀራችሁት ግን ለተራቡት ቤተ ሰቦቻችሁ እህል ትወስዱላቸዋላችሁ፤ ታናሽ ወንድማችሁን ግን ይዛችሁ መምጣት አለባችሁ፤ በዚህም የተናገራችሁት ቃል እውነተኛነት ይረጋገጣል፤ እናንተም ከመሞት ትተርፋላችሁ።” እነርሱም ይህንኑ ለመፈጸም ተስማሙ። እርስ በርሳቸውም፣ “ይኸው በወንድማችን ላይ ባደረስነው በደል ምክንያት ቅጣታችንን እየተቀበልን ነው። እርሱ እንደዚያ ተጨንቆ ስለ ሕይወቱ ሲማፀነን፣ እኛ አልሰማነውም ነበር፤ ይህ መከራ የደረሰብንም በዚሁ ምክንያት ነው” ተባባሉ። ሮቤልም መልሶ፣ “በዚህ ልጅ ላይ፣ ‘ክፉ ነገር አታድርጉ’ ብዬ አልነበረምን? እናንተ ግን አልሰማችሁኝም፤ ስለዚህም ደሙ ከእጃችን ይፈለጋል” አላቸው። ዮሴፍ የሚያነጋግራቸው በአስተርጓሚ ስለ ሆነ የሚነጋገሩትን እንደሚሰማቸው አላወቁም ነበር። ከፊታቸውም ዘወር ብሎ አለቀሰ፤ ከዚያም ወደ እነርሱ ተመልሶ እንደ ገና አነጋገራቸው፤ ስምዖንንም ከእነርሱ ለይቶ ዐይናቸው እያየ አሰረው። በስልቻዎቻቸው እህል እንዲሞሉላቸው፣ ብሩንም በእያንዳንዱ ሰው ስልቻ ውስጥ መልሰው እንዲያስቀምጡና ለጕዟቸው ስንቅ እንዲያሲዟቸው ዮሴፍ ትእዛዝ ሰጠ። ይህም ከተደረገላቸው በኋላ፣ እህላቸውን በአህዮቻቸው ጭነው ጕዟቸውን ቀጠሉ። በመንገድም ለዐዳር ሰፍረው ሳሉ፣ ከእነርሱ አንዱ ከያዘው እህል ላይ ለአህያው ለመስጠት ስልቻውን ሲፈታ፣ በስልቻው አፍ ላይ ብሩን አገኘ። እርሱም ወንድሞቹን፣ “ኧረ ብሬ ተመልሶልኛል፤ ይኸው ስልቻዬ ውስጥ አገኘሁት” አላቸው። ሁሉም ልባቸው በድንጋጤ ተሞልቶ እየተንቀጠቀጡ በመተያየት፣ “እግዚአብሔር ምን ሊያመጣብን ይሆን?” አሉ። በከነዓን ምድር ወዳለው ወደ አባታቸው ወደ ያዕቆብ ከደረሱ በኋላ፣ ያጋጠማቸውን ሁሉ እንዲህ ብለው ነገሩት፤ “የአገሩ ጌታ የሆነው ሰው ምድሪቱን እንደምንሰልል ቈጥሮን በቍጣ ተናገረን። እኛ ግን እንዲህ አልነው፤ ‘እኛ የታመንን ሰዎች እንጂ ሰላዮች አይደለንም። እኛ የአንድ አባት ልጆች የሆንን፣ ዐሥራ ሁለት ወንድማማቾች ነን፤ አንዱ የለም፤ ታናሽ ወንድማችን ግን ከአባታችን ጋራ በከነዓን ይገኛል።’ “ከዚህ በኋላ የአገሩ ጌታ የሆነው ሰው እንዲህ አለን፤ ‘ታማኝ ሰዎች መሆናችሁን የማውቀው በዚህ ነው፤ ከእናንተ መካከል አንዱን ወንድማችሁን እዚህ እኔ ዘንድ ትታችሁ የተቀራችሁት ለተራቡት ቤተ ሰቦቻችሁ እህል ይዛችሁላቸው ሂዱ። ነገር ግን ታናሽ ወንድማችሁን ወደ እኔ አምጡት። በዚያም ጊዜ ታማኝ ሰዎች እንጂ ሰላዮች አለመሆናችሁን ዐውቃለሁ፤ ወንድማችሁንም መልሼ እሰጣችኋለሁ፤ እናንተም በምድሪቱ እንደ ልብ ለመዘዋወር ትችላላችሁ።’ ” እህሉንም ሲዘረግፉ በየስልቾቻቸው ውስጥ ብራቸው እንደ ተቋጠረ ተገኘ፤ የእያንዳንዳቸውን የተቋጠረ ብር ሲያዩም፣ እነርሱም ሆኑ አባታቸው ደነገጡ። አባታቸው ያዕቆብም፣ “ያለ ልጅ እኮ አስቀራችሁኝ፤ ዮሴፍ የለም፤ ስምዖንም የለም፤ አሁን ደግሞ ብንያምን ልትወስዱ ትፈልጋላችሁ፤ ኧረ ምን ጕድ ነው የመጣብኝ!” አላቸው። በዚህ ጊዜ ሮቤል አባቱን፣ “መልሼ ባላመጣው፣ ሁለቱን ወንዶች ልጆቼን ግደላቸው፤ ኀላፊነቱን ለእኔ ተውልኝ፤ እኔው መልሼ አመጣዋለሁ” አለው። ያዕቆብም፣ “ልጄ ዐብሯችሁ ወደዚያ አይወርድም፤ ወንድሙ እንደሆን ሞቷል፤ የቀረው እርሱ ብቻ ነው። ይዛችሁት ስትሄዱ በመንገድ ላይ አደጋ ቢደርስበት፣ ሽበቴን በመሪር ሐዘን ወደ መቃብር ታወርዱታላችሁ” አላቸው።
ዘፍጥረት 42 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 42
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 42:1-38
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች