ዘፍጥረት 41:25-40

ዘፍጥረት 41:25-40 NASV

ዮሴፍም ለፈርዖን እንዲህ አለው፤ “ሁለቱም የፈርዖን ሕልሞች ተመሳሳይና አንድ ዐይነት ናቸው፤ እግዚአብሔር ወደ ፊት የሚያደርገውን ለፈርዖን ገልጦለታል። ሰባቱ የሚያማምሩ ላሞች፣ ሰባት ዓመታት ናቸው፣ ሰባቱም የሚያማምሩ የእሸት ዛላዎች ሰባት ዓመታት ናቸው፤ ሕልሙም አንድና ተመሳሳይ ነው። ከእነርሱም በኋላ ዐጥንታቸው የወጣ አስከፊ መልክ ያላቸው ሰባት ላሞች፣ ሰባት ዓመታት ናቸው፤ እንደዚሁም ፍሬ አልባ የሆኑትና በምሥራቅ ነፋስ ተመትተው የደረቁት ሰባት የእሸት ዛላዎች ሰባት የራብ ዓመታት ናቸው። “አስቀድሜ ለፈርዖን እንደ ተናገርሁት፣ እግዚአብሔር ወደ ፊት የሚያደርገውን ነገር ለፈርዖን ገልጦለታል። በመላው የግብጽ ምድር እጅግ የተትረፈረፈ ጥጋብ የሚሆንባቸው ሰባት ዓመታት ይመጣሉ። ከዚህ በኋላ ግን በተከታታይ ሰባት የራብ ዓመታት ይሆናሉ። የራቡ ዘመን አገሪቱን እጅግ ስለሚጐዳት፣ በግብጽ የነበረው ያለፈው የጥጋብ ዘመን ሁሉ ጨርሶ አይታወስም። ከጥጋቡ ዓመታት በኋላ የሚመጣው የራብ ዘመን እጅግ ጽኑ ከመሆኑ የተነሣ፣ ቀደም ሲል የነበረው የጥጋብ ዘመን ፈጽሞ ይረሳል። ሕልሙ ለፈርዖን በሁለት መልክ በድጋሚ መታየቱ፣ ነገሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቈረጠ ስለ ሆነ ነው፤ ይህንም እግዚአብሔር በቅርብ ጊዜ ይፈጽመዋል። “እንግዲህ ፈርዖን ብልኅና አስተዋይ ሰው ፈልጎ፣ በመላው የግብጽ ምድር ላይ አሁኑኑ ይሹም። እንደዚሁም በሰባቱ የጥጋብ ዓመታት ከሚገኘው ምርት፣ አንድ ዐምስተኛው እንዲሰበሰብ የሚያደርጉ ኀላፊዎችን ይሹም። እነርሱም በሚመጡት የጥጋብ ዓመታት ከሚገኘው ምርት ሁሉ ይሰብስቡ፤ በፈርዖንም ሥልጣን ሥር ያከማቹ፤ ለምግብ እንዲሆኑም በየከተማው ይጠበቁ። የሚከማቸው እህል፣ ወደ ፊት በግብጽ አገር ላይ ለሚመጣው የሰባት ዓመት ራብ መጠባበቂያ ይሁን፤ በዚህም ሁኔታ አገሪቱ በራብ አትጠፋም።” ዕቅዱንም ፈርዖንና ሹማምቱ ሁሉ መልካም ሆኖ አገኙት። ፈርዖንም፣ “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት እንደዚህ ያለ ሰው ማንን ልናገኝ እንችላለን?” ብሎ ጠየቃቸው። ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ስለ ገለጠልህ፣ እንደ አንተ ያለ አስተዋይና ብልኅ ሰው የለም። አንተ በቤተ መንግሥቴ የበላይ ትሆናለህ፤ ሕዝቤም ሁሉ ለሥልጣንህ ይገዛል፤ እኔ ከአንተ የምበልጠው በዙፋኔ ብቻ ይሆናል።”

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}