ዘፍጥረት 32:22-32

ዘፍጥረት 32:22-32 NASV

በዚያች ሌሊት ያዕቆብ ተነሣ፤ ሁለቱን ሚስቶቹን እንዲሁም ሁለቱን ሴት አገልጋዮቹንና ዐሥራ አንድ ልጆቹን ይዞ በያቦቅ መልካ ተሻገረ። ወንዙን አሻግሮ ከሸኛቸው በኋላ፣ ጓዙን ሁሉ ሰደደ። ያዕቆብ ግን ብቻውን እዚያው ቀረ፤ አንድ ሰውም እስኪነጋ ድረስ ሲታገለው ዐደረ። ያም ሰው ያዕቆብን ታግሎ ማሸነፍ እንዳቃተው በተረዳ ጊዜ፣ የጭኑን ሹልዳ ነካው፤ በግብግቡም የያዕቆብ ጭን ከመጋጠሚያው ላይ ተናጋ። በዚያ ጊዜ ሰውየው፣ “እንግዲህ መንጋቱ ስለ ሆነ ልቀቀኝና ልሂድ” አለው። ያዕቆብም፣ “ካልባረክኸኝ አልለቅህም” አለው። ሰውየውም፣ “ስምህ ማን ነው?” አለው። እርሱም፣ “ያዕቆብ ነው” አለ። ሰውየውም፣ “ከእግዚአብሔርም፣ ከሰዎችም ጋራ ታግለህ አሸንፈሃልና ከእንግዲህ ስምህ እስራኤል እንጂ፣ ያዕቆብ አይባልም” አለው። ያዕቆብም፣ “እባክህ ስምህን ንገረኝ” ብሎ ጠየቀው። ሰውየውም፣ “ስሜን ለማወቅ ለምን ፈለግህ?” አለው፤ በዚያም ስፍራ ባረከው። ስለዚህ ያዕቆብ፣ “እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አይቼ እንኳ ሕይወቴ ተርፋለች” ሲል፣ የዚያን ቦታ ስም ጵኒኤል አለው። ጵኒኤልንም እንዳለፈ ፀሓይ ወጣችበት፤ እርሱም በጭኑ ምክንያት ያነክስ ነበር። ከዚህም የተነሣ የእስራኤል ልጆች እስከ ዛሬ ድረስ ሹልዳን ከጭኑ ጋራ የሚያገናኘውን ሥጋ አይበሉም፤ ምክንያቱም በጭኑ መጋጠሚያ ላይ ያለው የያዕቆብ ሹልዳ ተነክቶ ነበር።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}