ራሔል ለያዕቆብ አንድም ልጅ እንዳልወለደችለት ባየች ጊዜ በእኅቷ ቀናች። ስለዚህ ያዕቆብን፣ “ልጅ ስጠኝ፤ አለዚያ እሞታለሁ” አለችው። ያዕቆብም ራሔልን ተቈጥቶ “እኔ እንዳትወልጂ ያደረገሽን እግዚአብሔርን መሰልኹሽን?” አላት። እርሷም፣ “እነሆ፤ አገልጋዬ ባላ አለችልህ፤ ልጆች እንድትወልድልኝና እኔም ደግሞ በርሷ አማካይነት ልጆች እንዳገኝ ከርሷ ጋራ ተኛ” አለችው። ስለዚህም አገልጋይዋን ባላን ሚስት እንድትሆነው ሰጠችው፤ ያዕቆብም ዐብሯት ተኛ፤ እርሷም ፀነሰች፤ ለያዕቆብም ወንድ ልጅ ወለደችለት። ራሔልም፣ “እግዚአብሔር ፈርዶልኛል፣ ልመናዬንም ሰምቶ ወንድ ልጅ ሰጥቶኛል” አለች። ስለዚህ ስሙን ዳን ብላ አወጣችለት። የራሔል አገልጋይ ባላ እንደ ገና ፀነሰች፤ ለያዕቆብም ሁለተኛ ወንድ ልጅ ወለደች። ራሔልም፣ “እኅቴን ብርቱ ትግል ገጥሜ አሸነፍሁ” አለች፤ ስሙንም ንፍታሌም ብላ አወጣችለት። ልያም ልጅ መውለድ ማቆሟን እንደ ተረዳች፣ አገልጋይዋን ዘለፋን ሚስት እንድትሆነው ለያዕቆብ ሰጠችው። የልያ አገልጋይ ዘለፋም ለያዕቆብ ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ልያም፣ “ምን ዐይነት መታደል ነው” አለች፤ ስሙንም ጋድ ብላ አወጣችለት። የልያም አገልጋይ ዘለፋ፤ ለያዕቆብ ሁለተኛ ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ልያም፣ “ምንኛ ደስተኛ ሆንሁ ከእንግዲህ ሴቶች ደስተኛዋ ይሉኛል” አለች፤ ስሙንም አሴር ብላ አወጣችለት። ስንዴ በሚታጨድበት ወቅት፣ ሮቤል ወደ ሜዳ ወጣ፤ እንኮይም አግኝቶ ለእናቱ ለልያ አመጣላት። ራሔልም ልያን፣ “እባክሽን ልጅሽ ካመጣልሽ እንኮይ ስጪኝ” አለቻት። ልያም፣ “ባሌን የቀማሽኝ አነሰና የልጄን እንኮይ ደግሞ ልትወስጂ አማረሽ?” አለቻት። ራሔልም፣ “ስለ ልጅሽ እንኮይ ዛሬ ከአንቺ ጋራ ይደር” አለቻት። በዚያች ምሽት ያዕቆብ ከዕርሻ ሲመለስ፣ ልያ ወጥታ ተቀበለችውና፣ “በልጄ እንኮይ ስለ ተከራየሁህ የዛሬው ዐዳርህ ከእኔ ጋራ ነው” አለችው፤ ያዕቆብም በዚያች ሌሊት ከርሷ ጋራ ዐደረ። እግዚአብሔር የልያን ጸሎት ሰማ፤ ፀነሰች፤ ለያዕቆብም ዐምስተኛውን ወንድ ልጅ ወለደች። ልያም፣ “አገልጋዬን ለባሌ በመስጠቴ እግዚአብሔር ክሶኛል” አለች፤ ስሙንም ይሳኮር ብላ አወጣችለት። ልያ አሁንም ደግማ ፀነሰች፤ ለያዕቆብም ስድስተኛውን ወንድ ልጅ ወለደች። እርሷም፣ “እግዚአብሔር በከበረ ስጦታ ዐድሎኛል፣ ስድስት ወንዶች ልጆች ስለ ወለድሁለት፣ ከእንግዲህ ባሌ አክብሮ ይይዘኛል”። አለች፤ ስሙንም ዛብሎን አለችው። ከዚያም በኋላ ሴት ልጅ ወለደች፤ ስሟንም ዲና አለቻት። እግዚአብሔርም ራሔልን ዐሰባት፤ ልመናዋንም ሰምቶ ማሕፀኗን ከፈተላት። ከዚያም ፀንሳ፣ ወንድ ልጅ ወለደችና “እግዚአብሔር ዕፍረቴን አስወገደልኝ” አለች፤ ስሙንም፣ “እግዚአብሔር ሌላ ወንድ ልጅ ጨምሮ ይስጠኝ” ስትል፣ ዮሴፍ አለችው።
ዘፍጥረት 30 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 30
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 30:1-24
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች