ዘፍጥረት 28:1-16

ዘፍጥረት 28:1-16 NASV

ይሥሐቅ ያዕቆብን አስጠርቶ ከመረቀው በኋላ፣ እንዲህ ሲል አዘዘው፤ “ምንም ቢሆን ከነዓናዊት ሴት አታግባ። አሁኑኑ ተነሥተህ በሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ወደሚኖረው፣ ወደ እናትህ አባት ወደ ባቱኤል ቤት ሂድ፤ እዚያም ከአጎትህ ከላባ ሴቶች ልጆች መካከል አንዲቷን አግባ። ሁሉን ቻይ አምላክ ይባርክህ፤ ብዙ ሕዝብ እስክትሆን ድረስ ልጆች አፍራ፤ ዘርህን ያብዛው። እግዚአብሔር ለአብርሃም ሰጥቶ የነበረውን አንተም በስደት የምትኖርበትን ይህችን ምድር ርስት አድርጎ ያወርስህ ዘንድ፣ ለአብርሃም የሰጠውን በረከት ለአንተና ለዘርህ ይስጥ።” ይሥሐቅም ያዕቆብን በሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ወደሚኖረው፣ የያዕቆብና የዔሳው እናት የርብቃ ወንድም ወደ ሆነው ወደ ሶርያዊው የባቱኤል ልጅ ወደ ላባ ላከው። ዔሳው፣ ይሥሐቅ ያዕቆብን መርቆ ሚስት እንዲያገባ ወደ ሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ እንደ ላከውና በባረከውም ጊዜ “ከነዓናዊት ሴት አታግባ” ብሎ ትእዛዝ እንደ ሰጠው ሰማ። ያዕቆብ የአባት የእናቱን ፈቃድ ለመፈጸም፣ ወደ መስጴጦምያ መሄዱንም ተረዳ። በዚህም የከነዓናውያን ሴቶች በአባቱ በይሥሐቅ ዘንድ የቱን ያህል የተጠሉ መሆናቸውን ተገነዘበ፤ ስለዚህም ወደ እስማኤል ሄደ፣ የአብርሃም ልጅ እስማኤል የወለዳትን፣ የነባዮትን እኅት ማዕሌትን በሚስቶቹ ላይ ተጨማሪ አድርጎ አገባ። ያዕቆብ ከቤርሳቤህ ተነሥቶ ወደ ካራን ሄደ። ወደ አንድ ስፍራ እንደ ደረሰም ፀሓይዋ ጠልቃ ስለ ነበር፣ ዐዳሩን በዚያ አደረገ፤ በአቅራቢያው ከነበሩትም ድንጋዮች አንዱን ተንተርሶ ተኛ። በሕልሙም፣ ጫፉ ሰማይ የሚደርስ መሰላል በምድር ላይ ቆሞ፣ በላዩም የእግዚአብሔር መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ አየ። እግዚአብሔርም ከጫፉ ላይ ቆሞ እንዲህ አለ፤ “የአባትህ የአብርሃም አምላክ፣ የይሥሐቅ አምላክ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ የተኛህበትን ምድር ለአንተና ለዘርህ እሰጣለሁ። ዘርህ እንደ ምድር አሸዋ ይበዛል፤ በምዕራብና በምሥራቅ፣ በሰሜንና በደቡብ ትስፋፋለህ፤ የምድርም ሕዝቦች ሁሉ በአንተና በዘርህ አማካይነት ይባረካሉ። እኔ ከአንተ ጋራ ነኝ፤ በምትሄድበት ስፍራ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፤ ወደዚህችም ምድር እመልስሃለሁ፤ የሰጠሁህን ተስፋ እስከምፈጽምልህ ድረስ አልተውህም።” ያዕቆብም ከእንቅልፉ ሲነቃ፣ “በእውነት እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ አለ፤ እኔ ግን ይህን አላወቅሁም ነበር” አለ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}