ይሥሐቅ አርጅቶ፣ ዐይኖቹ ደክመው ማየት በተሳናቸው ጊዜ፣ ታላቁን ልጁን ዔሳውን ጠርቶ፣ “ልጄ ሆይ” አለው። እርሱም፣ “እነሆ፤ አለሁ” አለ። ይሥሐቅም እንዲህ አለ፤ “ይኸው እኔ አርጅቻለሁ፤ የምሞትበትንም ቀን አላውቅም ስለዚህ የዐደን መሣሪያህን፦ የፍላጻ ኰረጆህንና ቀስትህን ይዘህ ወደ ዱር ሂድ፤ አድነህም አምጣልኝ። ከመሞቴ በፊት እንድመርቅህ የምወድደውን ዐይነት ጣዕም ያለው ምግብ አዘጋጅተህ አብላኝ።” ይሥሐቅ ለልጁ የተናገረውን ርብቃ ትሰማ ስለ ነበር፣ ዔሳው የታዘዘውን ለማምጣት ለዐደን እንደ ወጣ፣ ርብቃ ለልጇ ለያዕቆብ እንዲህ አለችው፤ “አባትህ ዔሳውን፣ ‘ከመሞቴ በፊት በእግዚአብሔር ፊት እንድመርቅህ፣ ጥሩ ጣዕም ያለው ምግብ እንድበላ አዘጋጅልኝ።’ ሲለው ሰምቻለሁ፤ ልጄ ሆይ፤ እንግዲህ የምነግርህን በጥሞና ስማኝ፤ የምልህንም አድርግ። ተነሣና ወደ መንጋው ሄደህ ሁለት ፍርጥም ያሉ የፍየል ጠቦቶች አምጣልኝ፤ እኔም አባትህ የሚወድደውን ዐይነት ምግብ አዘጋጅለታለሁ፤ እርሱም ከመሞቱ በፊት እንዲመርቅህ ይዘህለት ግባና ይብላ።” ያዕቆብም እናቱን ርብቃን እንዲህ አላት፤ “ወንድሜ ዔሳው ሰውነቱ ጠጕራም ነው፤ የእኔ ገላ ግን ለስላሳ ነው። ታዲያ፣ አባቴ ቢዳስሰኝ እንዳታለልሁት ያውቃል፤ ይህ ከሆነ ደግሞ፣ በምርቃት ፈንታ ርግማን አተርፋለሁ ማለት ነው።” እናቱም፣ “ልጄ ሆይ፤ የአንተ ርግማን በእኔ ላይ ይድረስ፤ ግድ የለህም፤ እንደ ነገርሁህ ሄደህ ጠቦቶቹን አምጣልኝ” አለችው። እርሱም ሄዶ ጠቦቶቹን ለእናቱ አመጣላት፤ እርሷም ልክ አባቱ እንደሚወድደው ዐይነት አጣፍጣ ጥሩ ምግብ አዘጋጀችለት። ከዚያም ርብቃ በቤት ያስቀመጠችውን የታላቁን ልጇን የዔሳውን ምርጥ ልብስ አንሥታ ለታናሹ ልጇ ለያዕቆብ አለበሰችው። እንዲሁም የዐንገቱን ለስላሳ ክፍል የጠቦቶቹን ቈዳ አለበሰችው። ከዚያም ያሰናዳችውን ጣፋጭ መብልና እንጀራ ለያዕቆብ ሰጠችው። ያዕቆብም ወደ አባቱ ሄዶ፣ “አባቴ ሆይ” አለ፤ ይሥሐቅም፣ “እነሆ፤ አለሁ ልጄ፤ ለመሆኑ አንተ ማን ነህ?” አለው። ያዕቆብም አባቱን፣ “እኔ የበኵር ልጅህ ዔሳው ነኝ፤ ያዘዝኸኝን አድርጌአለሁ፤ እስኪ ቀና በልና እንድትመርቀኝ ዐድኜ ካመጣሁት ብላ” አለ። ይሥሐቅ ልጁን፣ “ልጄ ሆይ፤ ከመቼው ቀንቶህ መጣህ?” ሲል ጠየቀው። ያዕቆብም፣ “እግዚአብሔር አምላክህ አሳካልኝ” ብሎ መለሰለት። ይሥሐቅም ያዕቆብን፣ “ልጄ ሆይ፤ አንተ በርግጥ ልጄ ዔሳው መሆንህን እንዳውቅ፣ እስኪ ቀረብ በልና ልዳብስህ” አለው። ያዕቆብም ወደ አባቱ ወደ ይሥሐቅ ተጠጋ፤ አባቱም በእጁ እየዳሰሰው፣ “ይህ ድምፅ የያዕቆብ ድምፅ ነው፤ እጆቹ ግን የዔሳው እጆች ናቸው” አለ። እጆቹ እንደ ወንድሙ እንደ ዔሳው እጆች ጠጕራም ስለ ሆኑ፣ ይሥሐቅ ያዕቆብን ለይቶ ማወቅ አልቻለም፤ ስለዚህ ባረከው። ይሥሐቅም፣ “በርግጥ አንተ ልጄ ዔሳው ነህ?” ሲል ጠየቀው። ያዕቆብም፣ “አዎን፤ ነኝ” ብሎ መለሰ። ከዚያም፣ “በል እንግዲህ ልጄ፤ እንድመርቅህ፣ ዐድነህ ካመጣኸው አቅርብልኝና ልብላ” አለው። ያዕቆብም ምግቡን ለአባቱ አቀረበለት፤ የወይን ጠጅም አመጣለት፤ እርሱም በላ፤ ጠጣም። ከዚያም አባቱ ይሥሐቅ፣ ያዕቆብን፣ “ልጄ ሆይ፤ እስኪ ቀረብ በልና ሳመኝ” አለው። ያዕቆብም ቀርቦ ሳመው፤ ይሥሐቅ የያዕቆብን ልብስ ካሸተተ በኋላ እንዲህ ብሎ መረቀው፤ “እነሆ፤ የልጄ ጠረን፣ እግዚአብሔር እንደ ባረከው፣ እንደ መስክ መዐዛ ነው። እግዚአብሔር የሰማይን ጠል፣ የምድርንም በረከት፣ የተትረፈረፈ እህልና የወይን ጠጅ ይስጥህ። መንግሥታት ይገዙልህ፤ ሕዝቦችም ተደፍተው እጅ ይንሡህ፤ የወንድሞችህ ጌታ ሁን፤ የእናትህም ልጆች ተደፍተው እጅ ይንሡህ፤ የሚረግሙህ የተረገሙ ይሁኑ፤ የሚባርኩህ የተባረኩ ይሁኑ።” ይሥሐቅ ያዕቆብን መርቆ እንዳበቃ፣ ያዕቆብ ገና ከአባቱ ዘንድ ሳይወጣ ወዲያውኑ፣ ወንድሙ ዔሳው ከዐደን ተመለሰ። እርሱም ደግሞ ጣፋጭ ምግብ በማዘጋጀት ለአባቱ አቅርቦ፣ “አባቴ ሆይ፤ እንድትመርቀኝ፣ እስኪ ቀና በልና ካደንሁት ብላ” አለው። አባቱ ይሥሐቅም፣ “አንተ ደግሞ ማን ነህ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም፣ “እኔማ የበኵር ልጅህ ዔሳው ነኝ” አለው። በዚህ ጊዜ ይሥሐቅ ክፉኛ እየተንቀጠቀጠ፣ “ታዲያ ቀደም ሲል ዐድኖ ያመጣልኝ ማን ነበር? አንተ ከመምጣትህ በፊት በልቼ መረቅሁት፤ እርሱም በርግጥ የተባረከ ይሆናል” አለው። ዔሳው የአባቱን ቃል ሲሰማ፣ ድምፁን ከፍ በማድረግ ምርር ብሎ አለቀሰ፤ አባቱንም፣ “አባቴ ሆይ፤ እኔንም ደግሞ እባክህ መርቀኝ” አለው። ይሥሐቅም፣ “ወንድምህ መጥቶ አታልሎኝ ምርቃትህን ወስዶብሃል” አለው። ዔሳውም፣ “ይህ ሰው ያዕቆብ መባሉ ትክክል አይደለምን? እኔን ሲያታልለኝ ይህ ሁለተኛ ጊዜው ነው፤ መጀመሪያ ብኵርናዬን ወሰደብኝ፤ አሁን ደግሞ ምርቃቴን ቀማኝ” አለ። ቀጥሎም፣ “ታዲያ ለእኔ ያስቀረኸው ምንም ምርቃት የለም?” ብሎ ጠየቀ።
ዘፍጥረት 27 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 27
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 27:1-36
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች