ይሥሐቅ፣ ርብቃ መካን ስለ ነበረች ስለ እርሷ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰማ፤ ርብቃም ፀነሰች። ልጆቹም በማሕፀኗ ውስጥ እርስ በርሳቸው ይጋፉ ጀመር፤ እርሷም “ለምን እንዲህ ይሆንብኛል?” ብላ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ሄደች። እግዚአብሔርም እንዲህ አላት፤ “ሁለት ወገኖች በማሕፀንሽ አሉ፤ ሁለትም ሕዝቦች ከውስጥሽ ተለያይተው ይወጣሉ፤ አንደኛው ከሌላው ይበረታል፤ ታላቁም ለታናሹ ይገዛል” አላት። የመውለጃዋ ጊዜ ሲደርስም፣ እነሆ፤ በማሕፀኗ መንታ ወንዶች ልጆች ነበሩ። በመጀመሪያ የተወለደው መልኩ ቀይ፣ ሰውነቱም በሙሉ ጠጕር የለበሰ ነበር፤ ስለዚህ ስሙ ዔሳው ተባለ። ከዚያም ወንድሙ ተወለደ፤ በእጁም የዔሳውን ተረከዝ ይዞ ወጣ፤ ከዚህም የተነሣ ስሙ ያዕቆብ ተባለ። ርብቃ ልጆቿን ስትወልድ፣ ይሥሐቅ የስድሳ ዓመት ሰው ነበር። ልጆቹም ዐደጉ፤ ዔሳው ጐበዝ ዐዳኝ፣ የበረሓም ሰው ሆነ፤ ያዕቆብ ግን ጭምት፣ ከድንኳኑ የማይወጣ ሰው ነበር። ይሥሐቅ ከዐደን የመጣ ሥጋ ደስ ይለው ስለ ነበር፣ ዔሳውን ይወድደው ነበር፤ ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወድደው ነበር። አንድ ቀን ያዕቆብ ወጥ እየሠራ ሳለ ዔሳው እጅግ ተርቦ ከዱር መጣ። ዔሳውም ያዕቆብን፣ “ቶሎ በል፤ በጣም ርቦኛልና ከዚህ ቀይ ወጥ አብላኝ” አለው። ስለዚህም ስሙ ኤዶም ተባለ። ያዕቆብም፣ “በመጀመሪያ ብኵርናህን ሽጥልኝ” አለው። ዔሳውም፣ “እነሆ፤ ልሞት ደርሻለሁ፤ ታዲያ ብኵርናው ምን ያደርግልኛል!” አለ። ያዕቆብም ዔሳውን፣ “እንግዲያማ፣ አስቀድመህ ማልልኝ” አለው፤ ስለዚህም ማለለት፤ ብኵርናውንም ለያዕቆብ ሸጠለት። ያዕቆብም ለዔሳው እንጀራና የምስር ወጥ ሰጠው፤ እርሱም ከበላና ከጠጣ በኋላ ተነሥቶ ሄደ። ዔሳው ብኵርናውን እንዲህ አድርጎ አቃለላት።
ዘፍጥረት 25 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 25
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 25:21-34
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች