ዘፍጥረት 24:26-56

ዘፍጥረት 24:26-56 NASV

ሰውየውም ተደፍቶ ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ እንዲህም አለ፤ “ቸርነቱንና ታማኝነቱን ከጌታዬ ያላጓደለ፣ እኔንም ወደ ጌታዬ ዘመዶች ቤት የመራኝ፣ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን።” ልጅቷ ሮጣ ሄዳ፣ የሆነውን ሁሉ ለእናቷ ቤተ ሰቦች ነገረች። ርብቃም ላባ የተባለ ወንድም ነበራት፤ እርሱም ሰውየው ወዳለበት የውሃ ጕድጓድ ፈጥኖ ሄደ። እኅቱ ያደረገችውን የወርቅ ቀለበትና አምባሮች እንዳየ፣ እንዲሁም ርብቃ ሰውየው ያላትን ስትናገር እንደ ሰማ፣ ወዲያውኑ ወደ ሰውየው ሄደ፤ በምንጩም ዳር ከግመሎቹ አጠገብ ቆሞ አገኘው፤ እርሱንም “አንተ የእግዚአብሔር ቡሩክ ሆይ፤ ና፤ እዚህ ውጭ የቆምኸው ለምንድን ነው? እነሆ፤ ለአንተ ማረፊያ ለግመሎችህም ማደሪያ አዘጋጅቻለሁ” አለው። ሰውየው ከላባ ጋራ ወደ ቤት ሄደ፤ የግመሎቹ ጭነት ተራግፎ ገለባና ድርቈሽ ተሰጣቸው፤ ለርሱና ዐብረውት ለነበሩት ሰዎች የእግር ውሃ ቀረበላቸው። ለሰውየውም ማእድ ቀረበለት፤ እርሱ ግን፣ “የመጣሁበትን ጕዳይ ሳልናገር እህል አልቀምስም” አለ። ላባም፣ “ዕሺ፤ ተናገር” አለው። እርሱም እንዲህ አለ፤ “እኔ የአብርሃም አገልጋይ ነኝ፤ እግዚአብሔር ጌታዬን እጅግ ባርኮታል፤ እርሱም በልጽጓል፤ በጎችና ከብቶች፣ ብርና ወርቅ፣ ወንድና ሴት አገልጋዮች፣ ግመሎችና አህዮች ሰጥቶታል። የጌታዬ ሚስት ሣራ በስተርጅናዋ ወንድ ልጅ ወልዳለታለች፤ ጌታዬም ያለውን ሀብት ሁሉ ለልጁ ሰጥቶታል። ጌታዬ እንዲህ ሲል አማለኝ፤ ‘ከዚህ ከምኖርበት አገር፣ ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች ጋራ ልጄን አታጋባው፤ ነገር ግን ወደ አባቴ ቤት፣ ወደ ገዛ ወገኖቼ ሄደህ ለልጄ ሚስት አምጣለት።’ “እኔም ጌታዬን፣ ‘ሴቲቱ ከእኔ ጋራ ወደዚህ ለመምጣት ባትፈቅድስ?’ ብዬ ጠየቅሁት። “እርሱም እንዲህ አለኝ፤ ‘አካሄዴን በፊቱ ያደረግሁ እግዚአብሔር መልአኩን ከአንተ ጋራ ይልካል፤ ከገዛ ወገኖቼና ከአባቴ ቤት፣ ለልጄ ሚስት እንድታመጣለት መንገድህን ያቃናል። ወደ ወገኖቼ ከሄድህ፣ ከመሐላው የተፈታህ ትሆናለህ፤ እነርሱ እንኳ ልጅቱን አንሰጥም ቢሉህ፣ ከመሐላው ንጹሕ ትሆናለህ’ አለኝ። “እኔም ዛሬ ወደ ውሃው ጕድጓድ ስደርስ እንዲህ ብዬ ጸለይሁ፤ ‘የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ፈቃድህ ቢሆን የመጣሁበትን ጕዳይ አቃናልኝ፤ እነሆ፤ በምንጩ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ ውሃ ልትቀዳ የምትመጣውን ኮረዳ፣ “ከእንስራሽ ውሃ አጠጪኝ” ስላት፣ “ዕሺ ጠጣ፤ ለግመሎችህም እቀዳላቸዋለሁ” የምትለኝ እርሷ እግዚአብሔር ለጌታዬ ልጅ የመረጣት ትሁን።’ “በልቤ የምጸልየውን ጸሎት ገና ሳልጨርስ፣ ርብቃ እንስራዋን በትከሻዋ ላይ አድርጋ ብቅ አለች፤ ወደ ምንጩም ወርዳ ውሃ ቀዳች። እኔም፣ ‘እባክሽ፤ ውሃ አጠጪኝ’ አልኋት። “እርሷም ፈጥና እንስራዋን ከትከሻዋ አውርዳ፣ ‘ጠጣ፤ ግመሎችህንም አጠጣለሁ’ አለች። እኔም ጠጣሁ፤ ግመሎቹንም አጠጣች። “ለመሆኑ ‘የማን ልጅ ነሽ’ ብዬ ጠየቅኋት። “እርሷም፣ ‘ሚልካ ለናኮር የወለደችለት፣ የባቱኤል ልጅ ነኝ’ አለችኝ። “ከዚያም ቀለበቱን አደረግሁላት፤ አምባሩንም በእጇ አስገባሁላት። ተደፍቼም ለእግዚአብሔር ሰገድሁ፤ ለጌታዬ ወንድም የልጅ ልጅ የሆነችውን ቈንጆ፣ ለጌታዬ ልጅ እንዳገኝለት በቀና መንገድ የመራኝን የጌታዬ የአብርሃምን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገንሁ። እንግዲህ አሁን ለጌታዬ በጎነትና ታማኝነት የምታሳዩ ከሆነ ሐሳባችሁን አስታውቁኝ፤ ካልሆነ ግን ቍርጡን ንገሩኝና የምሄድበትን ልወስን።” ላባና ባቱኤል እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “ነገሩ ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ በዚህም ሆነ በዚያ ምንም ማለት አንችልም። ርብቃ ይቻትልህ፤ ይዘሃት ሂድ፤ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው ለጌታህ ልጅ ሚስት ትሁነው።” የአብርሃም አገልጋይ ያሉትን በሰማ ጊዜ በምድር ላይ ተደፍቶ ለእግዚአብሔር ሰገደ። ከዚያም የወርቅና የብር ጌጣጌጥ፣ እንዲሁም ልብሶች አውጥቶ ለርብቃ ሰጣት፤ ደግሞም ለወንድሟና ለእናቷ ከፍ ያለ ዋጋ ያላቸው ስጦታዎች ሰጣቸው። እርሱና ዐብረውት የነበሩ ሰዎችም በልተው፣ ጠጥተው እዚያው ዐደሩ። በማግስቱም ጧት ሲነሡ፣ የአብርሃም አገልጋይ፣ “እንግዲህ ወደ ጌታዬ እንድመለስ አሰናብቱኝ” አለ። ወንድሟና እናቷም፣ “ልጅቷ ከእኛ ጋራ ቢያንስ ዐሥር ቀን ያህል ትቈይና ከዚያ በኋላ ልትሄድ ትችላለች።” ብለው መለሱ። እርሱ ግን፣ “እግዚአብሔር መንገዴን አቅንቶልኛልና አታዘግዩኝ፤ ወደ ጌታዬ እንድመለስ አሰናብቱኝ” አላቸው።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}