ከዚህ ሁሉ በኋላ እግዚአብሔር አብርሃምን ፈተነው፤ “አብርሃም!” አለው። እርሱም “አቤቱ አለሁ” አለ። እግዚአብሔርም፣ “የምትወድደውን አንዱን ልጅህን፣ ይሥሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያ ምድር ሂድ፤ እኔ በማመለክትህ በአንዱ ተራራ ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው” አለው። በማግስቱም ጧት አብርሃም ማልዶ ተነሣ፤ አህያውን ጭኖ፣ ሁለት አገልጋዮቹንና ልጁን ይሥሐቅን ይዞ፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚበቃውን ዕንጨት ከቈረጠ በኋላ እግዚአብሔር ወዳመለከተው ቦታ ለመሄድ ጕዞውን ጀመረ፤ በሦስተኛው ቀን አብርሃም ቀና ብሎ ቦታውን ከሩቅ ተመለከተ፤ አገልጋዮቹንም “እናንተ አህያውን ይዛችሁ እዚህ ቈዩን፤ እኔና ልጄ ግን ወደዚያ ሄደን ለእግዚአብሔር ሰግደን እንመለሳለን” አላቸው። አብርሃም ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን ዕንጨት ወስዶ፣ ልጁን ይሥሐቅን አሸከመው፤ እሳቱንና ቢላዋውንም ራሱ ያዘ። ሁለቱም ዐብረው ሄዱ። ይሥሐቅም አባቱን አብርሃምን፣ “አባቴ ሆይ” አለው። አብርሃምም፣ “እነሆኝ፤ አለሁ ልጄ” አለው። ይሥሐቅም፣ “እሳቱና ዕንጨቱ ይኸው፤ ነገር ግን የሚቃጠለው መሥዋዕት በግ የት አለ?” ብሎ ጠየቀ። አብርሃምም፣ “ልጄ ሆይ፤ ለሚቃጠለው መሥዋዕት የሚሆነውን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል” አለው። ሁለቱም ዐብረው ጕዟቸውን ቀጠሉ። እግዚአብሔር ወደ አመለከተው ቦታ እንደ ደረሱ፣ አብርሃም መሠዊያ ሠራ፤ በላዩም ላይ ዕንጨት ረበረበ፤ ልጁን ይሥሐቅንም አስሮ በመሠዊያው ዕንጨት ላይ አጋደመው። ከዚያም ልጁን ለማረድ እጁን ዘርግቶ ቢላዋውን አነሣ። የእግዚአብሔር መልአክ ግን ከሰማይ፣ “አብርሃም! አብርሃም!” ብሎ ጠራው። አብርሃምም፣ “እነሆ፤ አለሁ” አለ። እርሱም፣ “እጅህን በብላቴናው ላይ አታሳርፍ፤ ምንም ጕዳት አታድርስበት፤ እነሆ፤ እግዚአብሔርን እንደምትፈራ ተረድቻለሁ፤ ልጅህን፣ ያውም አንዱን ልጅህን ለእኔ ለመስጠት አልሣሣህምና” አለው። አብርሃም ቀና ብሎ ተመለከተ፤ በቍጥቋጦ መካከልም ቀንዶቹ የተጠላለፉ አንድ አውራ በግ ከበስተኋላው አየ፤ ወደዚያው ሄዶ በጉን አመጣና የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ሠዋው። ከዚህም የተነሣ አብርሃም የዚያን ስፍራ ስም፣ “እግዚአብሔር ያዘጋጃል” ብሎ ጠራው፤ እስከ ዛሬም ድረስ፣ “በእግዚአብሔር ተራራ ላይ ይዘጋጃል” ይባላል። የእግዚአብሔርም መልአክ አብርሃምን ከሰማይ ዳግመኛ ጠራው፤ እንዲህም አለው፤ “እግዚአብሔርም በራሴ ማልሁ አለ፤ አንዱን ልጅህን ለእኔ ለመስጠት አልሣሣህምና፣ በርግጥ እባርክሃለሁ፤ ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት፣ እንደ ባሕር ዳር አሸዋም አበዛዋለሁ። ዘሮችህም የጠላቶቻቸውን ደጆች ይወርሳሉ፤ አሕዛብ ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ፤ ቃሌን ሰምተሃልና።” ከዚያም አብርሃም ወደ አገልጋዮቹ ተመለሰ፤ ተያይዘውም ወደ ቤርሳቤህ ሄዱ፤ አብርሃምም በቤርሳቤህ ኖረ። ከዚህ በኋላ እንዲህ ተብሎ ለአብርሃም ተነገረው፤ “ሚልካም ደግሞ የልጆች እናት ሆናለች፤ ለወንድምህም ለናኮር ወንዶች ልጆችን ወልዳለች። እነርሱም የበኵር ልጁ ዑፅና ወንድሙ ቡዝ፣ የአራም አባት ቀሙኤል፣ ኮዛት፣ ሐዞ፣ ፊልዳሥ፣ የድላፍና ባቱኤል ናቸው።” ባቱኤልም ርብቃን ወለደ። ሚልካ ለአብርሃም ወንድም ለናኮር የወለደችለት እነዚህ ስምንት ወንዶች ልጆች ናቸው። ከእነዚህም ሌላ የናኮር ቁባት ሬናሕ ደግሞ ጥባሕ፣ ገአም፣ ተሐሽና ሞክሳ የተባሉ ወንዶች ልጆች ወለደችለት።
ዘፍጥረት 22 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 22
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 22:1-24
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች