ዘፍጥረት 2:8-17

ዘፍጥረት 2:8-17 NASV

እግዚአብሔር አምላክ በምሥራቅ፣ በዔድን የአትክልት ስፍራ አዘጋጀ፤ ያበጀውንም ሰው በዚያ አኖረው። እግዚአብሔር አምላክም ለዐይን የሚያስደስት ለመብልም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ከምድር አበቀለ፤ በአትክልቱ ቦታ መካከልም የሕይወት ዛፍ ነበረ፤ እንዲሁም መልካምና ክፉን መለየት የሚያስችለው የዕውቀት ዛፍ ነበረ። የአትክልት ስፍራውን የሚያጠጣ ወንዝ ከዔድን ይፈስስ ነበር፤ ከዚያም በአራት ተከፍሎ ይወጣ ነበር። የመጀመሪያው፣ ወርቅ በሚገኝበት በኤውላጥ ምድር ዙሪያ ሁሉ የሚፈስሰው የፊሶን ወንዝ ነው። ኤውላጥ ምርጥ የሆነ ወርቅ፣ መልካም መዐዛ ያለው ከርቤና የከበረ ድንጋይ የሚገኙበት ምድር ነው። ሁለተኛው፣ በኢትዮጵያ ምድር ዙሪያ ሁሉ የሚፈስሰው የግዮን ወንዝ ነው። ሦስተኛው፣ ከአሦር በስተምሥራቅ የሚፈስሰው የጤግሮስ ወንዝ ሲሆን፣ አራተኛው የኤፍራጥስ ወንዝ ነው። እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ወስዶ እንዲያለማትና እየተንከባከበ እንዲጠብቃት በዔድን የአትክልት ስፍራ አስቀመጠው። እግዚአብሔር አምላክ ሰውን እንዲህ በማለት አዘዘው፤ “በአትክልት ስፍራው ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ ትበላለህ። ነገር ግን መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ፤ ምክንያቱም ከርሱ በበላህ ቀን በርግጥ ትሞታለህ።”

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}