የሰማያትና የምድር፣ በውስጣቸውም ያሉት ሁሉ አፈጣጠር በዚህ ሁኔታ ተከናወነ። እግዚአብሔር ይሠራ የነበረውን ሥራውን በሰባተኛው ቀን ላይ ፈጽሞ ነበር፤ ስለዚህ ይሠራ ከነበረው ሥራው ሁሉ በሰባተኛው ቀን ዐረፈ። እግዚአብሔር ሰባተኛውን ቀን ባረከው፤ ቀደሰውም፤ ካከናወነው የመፍጠር ሥራው ሁሉ ያረፈው በሰባተኛው ቀን ነውና። እግዚአብሔር አምላክ ሰማያትንና ምድርን በፈጠረ ጊዜ የተከናወኑት እንደዚህ ነበረ፤ እግዚአብሔር አምላክ ሰማያትንና ምድርን ሲፈጥር፣ የሜዳ ቡቃያ ገና በምድር ላይ አልታየም፤ የሜዳ ተክልም ገና አልበቀለም፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር አምላክ በመሬት ላይ ገና ዝናብ አላዘነበም ነበር፤ ምድርንም የሚያለማ ሰው አልነበረም። ነገር ግን ውሃ ከመሬት እየመነጨ የምድርን ገጽ ያረሰርስ ነበር። እግዚአብሔር አምላክ ከምድር ዐፈር ወስዶ ሰውን አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ። እግዚአብሔር አምላክ በምሥራቅ፣ በዔድን የአትክልት ስፍራ አዘጋጀ፤ ያበጀውንም ሰው በዚያ አኖረው። እግዚአብሔር አምላክም ለዐይን የሚያስደስት ለመብልም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ከምድር አበቀለ፤ በአትክልቱ ቦታ መካከልም የሕይወት ዛፍ ነበረ፤ እንዲሁም መልካምና ክፉን መለየት የሚያስችለው የዕውቀት ዛፍ ነበረ። የአትክልት ስፍራውን የሚያጠጣ ወንዝ ከዔድን ይፈስስ ነበር፤ ከዚያም በአራት ተከፍሎ ይወጣ ነበር። የመጀመሪያው፣ ወርቅ በሚገኝበት በኤውላጥ ምድር ዙሪያ ሁሉ የሚፈስሰው የፊሶን ወንዝ ነው። ኤውላጥ ምርጥ የሆነ ወርቅ፣ መልካም መዐዛ ያለው ከርቤና የከበረ ድንጋይ የሚገኙበት ምድር ነው። ሁለተኛው፣ በኢትዮጵያ ምድር ዙሪያ ሁሉ የሚፈስሰው የግዮን ወንዝ ነው። ሦስተኛው፣ ከአሦር በስተምሥራቅ የሚፈስሰው የጤግሮስ ወንዝ ሲሆን፣ አራተኛው የኤፍራጥስ ወንዝ ነው።
ዘፍጥረት 2 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 2
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 2:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች