አብራምም ከዚያ ተነሥቶ ወደ ኔጌብ ሄደ። በዚያም ምድር ጽኑ ራብ ገብቶ ነበር፤ ከዚህም የተነሣ አብራም ለጥቂት ጊዜ በዚያ ለመኖር ወደ ግብጽ ወረደ። ግብጽ ለመግባት ጥቂት ሲቀረው አብራም ሚስቱን ሦራን እንዲህ አላት፤ “መቼም አንቺ ውብ ሴት መሆንሽን ዐውቃለሁ፤ ግብጻውያን አንቺን በሚያዩበት ጊዜ፣ ‘ይህች ሚስቱ ናት’ ብለው እኔን ይገድላሉ፤ አንቺን ግን ይተዉሻል። ስለዚህ ለአንቺ ሲሉ እንዲንከባከቡኝ፣ ሕይወቴም እንድትተርፍ፣ ‘እኅቱ ነኝ’ በዪ።” አብራም በግብጽ አገር እንደ ደረሰ ግብጻውያን፣ ሦራ እጅግ ውብ ሴት እንደ ሆነች አዩ፤ የፈርዖንም ሹማምት ባዩአት ጊዜ፣ ለፈርዖን አድንቀው ነገሩት፤ ወደ ቤተ መንግሥትም ወሰዷት። በርሷም ምክንያት ፈርዖን አብራምን አክብሮ አስተናገደው፤ በጎችና ከብቶች፣ ተባዕትና እንስት አህዮች፣ ወንድና ሴት አገልጋዮች እንዲሁም ግመሎችን ሰጠው። እግዚአብሔርም በአብራም ሚስት በሦራ ምክንያት ፈርዖንንና ቤተ ሰዎቹን በጽኑ ደዌ መታቸው። ከዚያም ፈርዖን አብራምን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “ይህ ያደረግህብን ነገር ምንድን ነው? ‘ሚስትህ እንደ ሆነች ለምን አልነገርኸኝም?’ ለምን ‘እኅቴ ናት’ አልኸኝ? ሚስቴ ላደርጋት ነበር። በል አሁንም ሚስትህ ይህችው፤ ይዘሃት ሂድ!” ከዚያም ፈርዖን ስለ አብራም ለባለሟሎቹ ትእዛዝ ሰጠ፤ እነርሱም አብራምን ከሚስቱና ከንብረቱ ሁሉ ጋራ አሰናበቱት።
ዘፍጥረት 12 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 12
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 12:9-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች