ዘፍጥረት 1:10-31

ዘፍጥረት 1:10-31 NASV

እግዚአብሔር ደረቁን ምድር፣ “የብስ”፣ በአንድነት የተሰበሰበውን ውሃ፣ “ባሕር” ብሎ ጠራው። እግዚአብሔር ይህ መልካም እንደ ሆነ አየ። እግዚአብሔር፣ “ምድር ዕፀዋትንም፣ እንደየወገናቸው ዘር የሚሰጡ ተክሎችንና በምድር ላይ ዘር ያዘሉ ፍሬ የሚያፈሩ ዛፎችን እንደየወገናቸው ታብቅል” አለ፤ እንዳለውም ሆነ። ምድር ዕፀዋትን፣ እንደየወገናቸው ዘር የሚሰጡ ተክሎችንና በውስጣቸው ዘር ያለባቸው ፍሬ የሚያፈሩትን ዛፎች በየወገኑ አበቀለች። እግዚአብሔርም ይህ መልካም እንደ ሆነ አየ። መሸ፤ ነጋም፤ ሦስተኛ ቀን። ከዚያም እግዚአብሔር፣ “ቀኑን ከሌሊት እንዲለዩ፣ የዓመት ወቅቶች፣ ቀናትና ዓመታት የሚጀምሩበትንም እንዲያመለክቱ፣ ለምድር ብርሃን የሚሰጡ ልዩ ልዩ ብርሃናት በሰማይ ይሁኑ” አለ፤ እንዳለውም ሆነ። እግዚአብሔር፣ ለምድር ብርሃን ይሰጡ ዘንድ ሁለት ታላላቅ ብርሃናት አደረገ፤ ታላቁ ብርሃን በቀን እንዲሠለጥን፣ ታናሹ ብርሃን በሌሊት እንዲሠለጥን አደረገ። እንዲሁም ከዋክብትን አደረገ። ለምድር ብርሃን እንዲሰጡ እግዚአብሔር እነዚህን በሰማይ ጠፈር አኖራቸው። ይኸውም በቀንና በሌሊት እንዲሠለጥኑ፣ ብርሃንን ከጨለማ እንዲለዩ ነው። እግዚአብሔርም ይህ መልካም እንደ ሆነ አየ። መሸ፤ ነጋም፣ አራተኛ ቀን። እግዚአብሔር፣ “ውሆች ሕይወት ባላቸው በሕያዋን ፍጥረታት ይሞሉ፤ ወፎች ከምድር በላይ በሰማይ ጠፈር ይብረሩ” አለ። በዚህ መሠረት፣ እግዚአብሔር በባሕር ውስጥ የሚኖሩ ታላላቅ ፍጥረታትን፣ በውሃ ውስጥ የሚርመሰመሱ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች ሁሉ እንደየወገናቸው እንዲሁም ክንፍ ያላቸውን ወፎች ሁሉ እንደየወገናቸው ፈጠረ፤ እግዚአብሔርም ይህ መልካም እንደ ሆነ አየ። እግዚአብሔርም፣ “ብዙ ተባዙ፤ የባሕርንም ውሃ ሙሏት፤ ወፎችም በምድር ላይ ይብዙ” ብሎ ባረካቸው። መሸ፤ ነጋም፤ ዐምስተኛ ቀን። እግዚአብሔር፣ “ምድር ሕያዋን ፍጥረታትን እንደየወገናቸው፣ ከብቶችን፣ በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጥረታትንና የዱር እንስሳትን እያንዳንዱን እንደ ወገኑ ታስገኝ” አለ፤ እንዳለውም ሆነ። እግዚአብሔር የዱር እንስሳትን እንደየወገናቸው፣ ከብቶችን እንደየወገናቸው፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጥረታትን እንደየወገናቸው አደረገ። እግዚአብሔርም ይህ መልካም እንደ ሆነ አየ። እግዚአብሔር፣ “ሰውን በመልካችን፣ በአምሳላችን እንሥራ፤ በባሕር ዓሦች፣ በሰማይ ወፎች፣ በከብቶች፣ በምድር ሁሉ ላይ፣ እንዲሁም በምድር ላይ በሚሳቡ ፍጥረታት ሁሉ ላይ ሥልጣን ይኑራቸው” አለ። ስለዚህ እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። እግዚአብሔርም፣ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም፤ የባሕርን ዓሦች፣ የሰማይን ወፎች፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ፍጥረታትን ሁሉ ግዟቸው” ብሎ ባረካቸው። እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፤ “በምድር ላይ ያሉትን ዘር የሚሰጡ ተክሎችን ሁሉ፣ በፍሬአቸው ውስጥ ዘር ያለባቸውን ዛፎች ሁሉ ምግብ ይሆኑላችሁ ዘንድ ሰጥቻችኋለሁ። እንዲሁም ለምድር አራዊት ሁሉ፣ ለሰማይ ወፎች ሁሉ፣ በምድር ላይ ለሚንቀሳቀሱ ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ ማንኛውም ለምለም ተክል ምግብ እንዲሆናቸው ሰጥቻለሁ” እንዳለውም ሆነ። እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፤ እነሆም፣ እጅግ መልካም ነበረ። መሸ፤ ነጋም፤ ስድስተኛ ቀን።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}