ገላትያ 1:1-24

ገላትያ 1:1-24 NASV

ከሰዎች ወይም በሰው ከተላከው ሳይሆን፣ በኢየሱስ ክርስቶስና ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስ፤ ዐብረውኝም ካሉት ወንድሞች ሁሉ፤ በገላትያ ላሉት አብያተ ክርስቲያናት፦ ከአባታችን ከእግዚአብሔር፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ፣ ከዚህ ክፉ ዓለም ያድነን ዘንድ ስለ ኀጢአታችን ራሱን ሰጠ፤ ከዘላለም እስከ ዘላለም ለርሱ ክብር ይሁን። አሜን። በክርስቶስ ጸጋ የጠራችሁን እርሱን ትታችሁ፣ ወደ ተለየ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ መዞራችሁ ደንቆኛል፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ሌላ ወንጌል የለም። የሚያደነጋግሯችሁና የክርስቶስን ወንጌል ለማጣመም ጥረት የሚያደርጉ አንዳንድ ሰዎች አሉ። ነገር ግን እኛም ብንሆን ወይም የሰማይ መልአክ፣ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የተለየ ወንጌል ቢሰብክላችሁ እርሱ ለዘላለም የተረገመ ይሁን! ቀደም ብለን እንዳልነው፣ አሁንም ደግሜ እላለሁ፤ ማንም ከተቀበላችሁት ሌላ የተለየ ወንጌል ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን! አሁን እኔ ተቀባይነት ለማግኘት የምሻው በሰዎች ዘንድ ነው ወይስ በእግዚአብሔር ዘንድ? ወይስ ሰዎችን ደስ ለማሠኘት እየተጣጣርሁ ነው? ሰዎችን ደስ ለማሠኘት የምጥር ብሆን ኖሮ፣ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁ ነበር። ወንድሞች ሆይ፤ የሰበክሁላችሁ ወንጌል ሰው ሠራሽ አለመሆኑን እንድታውቁ እፈልጋለሁ፤ ከማንም ሰው አልተቀበልሁትም፤ ከማንም አልተማርሁትም፤ ይልቁንስ በመገለጥ ከኢየሱስ ክርስቶስ ተቀበልሁት። ቀድሞ በአይሁድ ሃይማኖት እንዴት እንደ ኖርሁ፣ የእግዚአብሔርንም ቤተ ክርስቲያን እንዴት በእጅጉ እንዳሳደድሁ፣ ለማጥፋትም እንዴት እንደ ጣርሁ ሰምታችኋል። በእኔ ዕድሜ ዘመን ከነበሩት ከብዙዎቹ አይሁድ ይበልጥ በአይሁድ ሃይማኖት እልቅ ነበር፤ ስለ አባቶቼም ወግ እጅግ ቀናተኛ ነበርሁ። ነገር ግን፣ ከእናቴ ማሕፀን ጀምሮ የለየኝና በጸጋው የጠራኝ እግዚአብሔር፣ በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ እንድሰብክ ልጁን በእኔ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፣ ከማንም ሥጋ ለባሽ ጋራ አልተማከርሁም፤ ከእኔ በፊት ሐዋርያት ወደሆኑትም ወደ ኢየሩሳሌም አልወጣሁም፤ ነገር ግን ወዲያው ወደ ዐረብ አገር ሄድሁ፤ በኋላም ወደ ደማስቆ ተመለስሁ። ከዚያም ከሦስት ዓመት በኋላ፣ ኬፋን አገኘው ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣሁ፤ ከርሱም ጋራ ዐሥራ ዐምስት ቀን ተቀመጥሁ። ነገር ግን ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በቀር፣ ከሐዋርያት ማንንም አላየሁም። በምጽፍላችሁ ነገር በእግዚአብሔር ፊት ሐሰት እንደማልናገር አስረግጬ እነግራችኋለሁ። ከዚያም በኋላ፣ ወደ ሶርያና ወደ ኪልቅያ አገር ሄድሁ። በክርስቶስ ያሉት የይሁዳ አብያተ ክርስቲያናትም ፊቴን አይተው አያውቁም ነበር፤ እነርሱ ግን፣ “ቀድሞ እኛን ሲያሳድድ የነበረ ሰው፣ ከዚህ በፊት ሊያጠፋው ይፈልግ የነበረውን እምነት አሁን እየሰበከ ነው” የሚለውን ወሬ ብቻ ሰምተው ነበር፤ በእኔም ምክንያት እግዚአብሔርን አመሰገኑ።