ዕዝራ በእግዚአብሔር ቤት ፊት ወድቆ በሚጸልይበት፣ በሚናዘዝበትና በሚያለቅስበት ጊዜ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች የሚገኙበት እጅግ ብዙ የእስራኤል ማኅበር በዙሪያው ተሰበሰበ፤ እነርሱም እንደዚሁ አምርረው አለቀሱ። ከዚያም ከኤላም ዘሮች አንዱ የሆነው የይሒኤል ልጅ ሴኬንያ ዕዝራን እንዲህ አለው፤ “በዙሪያችን ካሉት አሕዛብ፣ ባዕዳን ሴቶችን በማግባታችን ለአምላካችን ታማኞች ሆነን አልተገኘንም፤ ይህም ሆኖ አሁንም ለእስራኤል ተስፋ አለ። አሁንም እንደ ጌታዬ ምክርና የአምላካችንን ትእዛዝ እንደሚፈሩ ሰዎች እነዚህን ሴቶችና ልጆቻቸውን ለመስደድ በአምላካችን ፊት ቃል ኪዳን እንግባ፤ በሕጉም መሠረት ይፈጸም። ዕዝራ፣ ነገሩ በእጅህ ነው፤ ተነሥ! እኛም እንደግፍሃለን፤ በርትተህም አድርገው።” ዕዝራም ተነሥቶ አለቆቹ ካህናት፣ ሌዋውያንና እስራኤል ሁሉ የቀረበውን ሐሳብ እንዲፈጽሙ አስማላቸው፤ እነርሱም ማሉ። ከዚያም ዕዝራ ከእግዚአብሔር ቤት ፊት ተነሥቶ ወደ ኤልያሴብ ልጅ ወደ ዮሐናን ክፍል ገባ፤ ምርኮኞቹ ታማኝነታቸውን ከማጕደላቸው የተነሣ ያለቅስ ነበር፤ በዚያም ምግብ አልቀመሰም፤ ውሃም አልጠጣም። ከዚያም ምርኮኞቹ ሁሉ በኢየሩሳሌም እንዲሰበሰቡ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ዐዋጅ ተነገረ፤ ዐዋጁም በሦስት ቀን ውስጥ ያልመጣ ማንም ሰው በሹማምቱና በሽማግሌዎቹ ውሳኔ መሠረት ንብረቱ ሁሉ እንዲወረስ፣ ራሱም ከምርኮኞቹ ጉባኤ እንዲወገድ የሚያዝ ነበር። ስለዚህ በሦስት ቀን ውስጥ የይሁዳና የብንያም ሰዎች ሁሉ በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ፤ በዘጠነኛው ወር በሃያኛውም ቀን ሕዝቡ ሁሉ ስለ ወቅቱ ጕዳይና ስለ ከባዱ ዝናብ በመጨነቅ በእግዚአብሔር ቤት ፊት ባለው አደባባይ ተቀምጠው ነበር። ከዚያም ካህኑ ዕዝራ ተነሥቶ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ታማኞች አልነበራችሁም፤ በእስራኤል በደል ላይ በደል በመጨመር ባዕዳን ሴቶችን አገባችሁ። አሁንም የአባቶቻችሁን አምላክ እግዚአብሔርን አክብሩ፤ ፈቃዱን ፈጽሙ፤ በዙሪያችሁ ካሉት አሕዛብና ከባዕዳን ሚስቶቻችሁ ተለዩ።” ጉባኤውም ሁሉ እንዲህ ሲሉ በታላቅ ድምፅ መለሱ፤ “እውነት ብለሃል፤ ያልኸውን መፈጸም ይገባናል።
ዕዝራ 10 ያንብቡ
ያዳምጡ ዕዝራ 10
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዕዝራ 10:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች