ከዚያም ያ ሰው ወደ ቤተ መቅደሱ መግቢያ መልሶ አመጣኝ፤ ከቤተ መቅደሱ መድረክ ሥር ውሃ እየወጣ፣ ወደ ምሥራቅ ይፈስስ ነበር፤ ቤተ መቅደሱ ለምሥራቅ ትይዩ ነበርና። ውሃው ከቤተ መቅደሱ በስተ ደቡብ በኩል፣ በመሠዊያው ደቡብ በኩል፣ ሥር ሥሩን ይወርዳል። ከዚያም በሰሜኑ በር በማውጣት በውጭ አዙሮ በምሥራቅ አቅጣጫ ወዳለው የውጭ በር መራኝ፤ ውሃውም በደቡብ በኩል ይፈስስ ነበር። ያም ሰው የመለኪያውን ገመድ በእጁ ይዞ ወደ ምሥራቅ በመሄድ፣ አንድ ሺሕ ክንድ ለካ፤ ከዚያም እስከ ቍርጭምጭሚት በሚደርሰው ውሃ ውስጥ መራኝ፤ ቀጥሎም አንድ ሺሕ ክንድ ለካ፤ እስከ ጕልበት ወደሚደርስም ውሃ መራኝ፤ ከዚያም ሌላ አንድ ሺሕ ክንድ ለካ፤ እስከ ወገብ ወደሚደርስም ውሃ መራኝ። እንደ ገናም አንድ ሺሕ ክንድ ለካ፤ አሁን ግን ልሻገረው የማልችል ወንዝ ሆነ፤ ምክንያቱም ውሃው ስለ ሞላና ጥልቅ ስለ ነበረ፣ በዋና ካልሆነ በቀር በእግር ሊሻገሩት የማይቻል ነበረ። እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ይህን ታየዋለህን?” ሲል ጠየቀኝ። ከዚያም መልሶ ወደ ወንዙ ዳር መራኝ፤ እዚያም በደረስሁ ጊዜ፣ በወንዙ ግራና ቀኝ ብዙ ዛፍ አየሁ። እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “ይህ ውሃ ወደ ምሥራቅ ምድር ይፈስሳል፤ ወደ ባሕሩ ወደሚገባበት ወደ ዓረባ ይወርዳል፤ ወደ ባሕሩም ሲፈስስ፣ በዚያ የነበረው ውሃ ንጹሕ ይሆናል። ወንዙ በሚፈስስበት ስፍራ ሁሉ ብዙ ሕያዋን ፍጥረታት ይኖራሉ። ይህ ውሃ በዚያ ስለሚፈስስና ጨውማ የሆነውን ውሃ ንጹሕ ስለሚያደርገው፣ ዓሣ በብዛት ይኖራል፤ ስለዚህ ወንዙ በሚፈስስበት ስፍራ ሁሉ ማንኛውም ነገር በሕይወት ይኖራል። ዓሣ አጥማጆች በወንዙ ዳር ይቆማሉ፤ ከዓይንጋዲ እስከ ዓይንኤግላይም ድረስ ያለው ቦታ መረብ መዘርጊያ ይሆናል፤ ዓሣውም እንደ ታላቁ ባሕር ዓሣ፣ የተለያየ ዐይነት ይሆናል። ነገር ግን ረግረጉና ዕቋሪው ውሃ ንጹሕ አይሆንም፤ ጨው እንደ ሆነ ይቀራል። በወንዙም ዳርና ዳር፣ ፍሬ የሚያፈሩ የዛፍ ዐይነቶች ሁሉ ይበቅላሉ፤ ቅጠላቸው አይደርቅም፤ ፍሬ አልባም አይሆኑም። ከመቅደሱ የሚወጣው ውሃ ስለሚፈስላቸው በየወሩ ያፈራሉ፤ ፍሬአቸው ለምግብ፣ ቅጠላቸውም ለፈውስ ይሆናል።”
ሕዝቅኤል 47 ያንብቡ
ያዳምጡ ሕዝቅኤል 47
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሕዝቅኤል 47:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች