“አንተ፣ የሰው ልጅ ሆይ፤ አንድ የሸክላ ጡብ ወስደህ ከፊት ለፊትህ አስቀምጥ፤ የኢየሩሳሌምን ከተማ ካርታ ሥራበት። ከዚያም በወታደር እንደሚከበብ ክበባት፤ ምሽግ ሥራባት፤ ዐፈር ደልድልባት፤ ጦር ሰፈሮችን ቀብቅብባት፤ ቅጥር መደርመሻ ግንዶችንም በዙሪያዋ አስቀምጥባት። የብረት ምጣድ ወስደህ በአንተና በከተማዪቱ መካከል እንደ ብረት ቅጥር አቁመው፤ ፊትህንም ወደ እርሷ አዙር፤ የተከበበች ትሆናለች፤ አንተም ትከብባታለህ። ይህም ለእስራኤል ቤት ምልክት ይሆናል። “አንተ በግራ ጐንህ ተኛ፤ የእስራኤልም ቤት ኀጢአት በአንተ ላይ ይሁን፤ በዚህ ጐንህ በተኛህበት ቀን ቍጥር ኀጢአታቸውን ትሸከማለህ። እነርሱ ኀጢአት ባደረጉባቸው ዓመታት መጠን የቀን ቍጥር መድቤብሃለሁ። ስለዚህ ሦስት መቶ ዘጠና ቀን የእስራኤልን ቤት ኀጢአት ትሸከማለህ። “ይህን ከፈጸምህ በኋላ ደግሞ በቀኝ ጐንህ ተኝተህ የይሁዳን ቤት ኀጢአት ትሸከማለህ፤ ለእያንዳንዱ ዓመት አንድ አንድ ቀን በማድረግ አርባ ቀን መድቤብሃለሁ። ፊትህን ወደ ኢየሩሳሌም ከበባ ታዞራለህ፣ በዕራቍት ክንድህ ትንቢት ተናገርባት። የከበባህን ወራት እስክትፈጽም ድረስ ከአንዱ ጐን ወደ ሌላው መገላበጥ እንዳትችል በገመድ አስርሃለሁ። “ስንዴና ገብስ፣ ባቄላና ምስር እንዲሁም ዘንጋዳና አጃ ወስደህ በአንድ ሸክላ ውስጥ አስቀምጥ፤ ከዚያም ለራስህ እንጀራ ጋግር፤ ሦስት መቶ ዘጠና ቀን በጐንህ በምትተኛበት ጊዜ ትመገበዋለህ። በየቀኑ የምትበላውን እህል ሃያ ሃያ ሰቅል መዝነህ አስቀምጥ፤ በተወሰነ ጊዜ ትበላዋለህ፤ የምትጠጣውንም ውሃ አንድ ስድስተኛ ሂን ለክተህ አስቀምጥ፤ በተወሰነ ጊዜ ትጠጣዋለህ። የገብስ ዕንጎቻ እንደምትበላ አድርገህ ትበላለህ፤ የሰውንም ዐይነ ምድር አንድደህ በሕዝብ ፊት ጋግረው።” እግዚአብሔርም፣ “በዚህ ሁኔታ የእስራኤል ሕዝብ እነርሱን በምበትንበት በአሕዛብ መካከል ርኩስ ምግብ ይበላሉ” አለ። እኔም፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ወይኔ! ከቶ ረክሼ አላውቅም፤ ከልጅነቴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ጥንብ ወይም አውሬ የጣለውን በልቼ አላውቅም፤ ርኩስ ሥጋም በአፌ አልገባም” አልሁ። እርሱም፣ “መልካም ነው፤ በሰው ዐይነ ምድር ሳይሆን፤ እንጀራህን በከብት ኵበት እንድትጋግር ፈቅጄልሃለሁ” አለኝ። ደግሞም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ የኢየሩሳሌምን የምግብ ምንጭ አደርቃለሁ፤ ሕዝቡም የተወሰነ ምግብ በጭንቀት ይበላል፤ የተመጠነ ውሃም በሥጋት ይጠጣል። የምግብና የውሃ ዕጥረት ስለሚኖር፣ እርስ በርስ ሲተያዩ ይደነግጣሉ፤ ከኀጢአታቸውም የተነሣ መንምነው ይጠፋሉ።
ሕዝቅኤል 4 ያንብቡ
ያዳምጡ ሕዝቅኤል 4
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሕዝቅኤል 4:1-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች