ሕዝቅኤል 38:1-23

ሕዝቅኤል 38:1-23 NASV

ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን በማጎግ ምድር በሚገኘው፣ በሜሼኽና በቶቤል ዋና አለቃ በጎግ ላይ አድርግ፤ በርሱ ላይ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የሜሼኽና የቶቤል ዋና አለቃ ጎግ ሆይ፤ ተነሥቼብሃለሁ። ወደ ኋላ እመልስሃለሁ፤ መንጋጋህ ውስጥ መንጠቆ አስገብቼ ከመላው ሰራዊትህ ጋራ፣ ፈረሶችህን፣ ፈረሰኞችህን ከነሙሉ ትጥቃቸው፣ ትልቅና ትንሽ ሰይፍ የያዙትን ሁሉ፣ ሰይፋቸውንም የወለወሉትን ሁሉ አስወጣለሁ። ጋሻ የያዙና የራስ ቍር የደፉት ሁሉ፣ ፋርስ፣ ኢትዮጵያና ፉጥ ከእነርሱ ጋራ ይሆናሉ። ደግሞም ጎሜርን ከወታደሮቹ ጋራ፣ ራቅ ካለው ሰሜንም የቶጋርማን ቤት ከወታደሮቹ ሁሉ ጋራ ብዙ ሕዝቦችን ከአንተ ጋራ አስወጣለሁ። “ ‘አንተና በዙሪያህ የተሰበሰቡት ሁሉ ተነሡ፤ ተዘጋጁ፤ አንተም መሪያቸው ሁን። ከብዙ ቀን በኋላ ለጦርነት ትጠራለህ። በኋለኛው ዘመንም ከጦርነት ያገገመችውን፣ ሕዝቧ ከአያሌ አሕዛብ መካከል ወጥቶ የተሰበሰበውን፣ ለብዙ ጊዜ ባድማ በነበረው በእስራኤል ተራሮች ላይ የሰፈረውን ወገን ትወርራለህ። ከሕዝቦች መካከል ወጥተው፣ አሁን ሁሉም ያለ ሥጋት ይኖራሉ። አንተና ወታደሮችህ ሁሉ፣ ከአንተም ጋራ ያሉት ብዙ ሕዝቦች እንደ ማዕበል ትወጣላችሁ፤ ምድርን እንደሚሸፍን ደመናም ትሆናላችሁ። “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በዚያ ቀን ሐሳብ ወደ አእምሮህ ይመጣል፤ ክፋትንም ታውጠነጥናለህ። እንዲህም ትላለህ፤ “ቅጥር የሌላቸውን መንደሮች ምድር እወራለሁ፤ ሁሉም ያለ ቅጥር፣ ያለ በርና ያለ ብረት መወርወሪያ የሚኖረውን፣ ሰላማዊና ያለ ሥጋት የተቀመጠውን ሕዝብ እወጋለሁ፤ እዘርፋለሁ፤ እነጥቃለሁ፤ እንዲሁም ከአሕዛብ ተሰባስቦ እንደ ገና በሰፈረው፣ በከብትና በሸቀጥ በከበረው፣ በምድሪቱም መካከል በሚኖረው ሕዝብ ላይ እጄን አነሣለሁ።” ሳባና ድዳን፣ የተርሴስ ነጋዴዎችና መንደሮቿም ሁሉ እንዲህ ይሉሃል፤ “ልትዘርፍ መጣህን? ሰራዊትህን ያሰባሰብኸው ለመበዝበዝ፣ ወርቅና ብሩን አጋብሶ ለመሄድ፣ ከብቱንና ሸቀጡን ለመውሰድ፣ ብዙ ምርኮ ይዞ ለመመለስ ነውን?” ’ “ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ፤ ትንቢት ተናገር፤ ጎግንም እንዲህ በለው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በዚያ ቀን ሕዝቤ እስራኤል ያለ ሥጋት መቀመጡን ዐውቀህ አትንቀሳቀስምን? በስተሰሜን ርቆ ከሚገኘው ቦታ ትመጣለህ፤ አንተና ከአንተም ጋራ ብዙ ሕዝቦች፣ እጅግ ታላቅ ኀያል ሰራዊትም በፈረሶች ላይ ሆናችሁ ትመጣላችሁ። ምድርን እንደሚሸፍን ደመና ሆነህ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ትወጣለህ። ጎግ ሆይ፤ በፊታቸው ቅድስናዬን ስገልጥ ሕዝቦች እኔን ያውቁ ዘንድ በኋለኛው ዘመን በምድሬ ላይ አመጣሃለሁ። “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በቀደመው ዘመን በባሪያዎቼ በእስራኤል ነቢያት ስለ እርሱ የተናገርሁለት ያ ሰው አንተ አይደለህምን? በዚያ ወቅት አንተን በእነርሱ ላይ እንደማመጣባቸው ለብዙ ዓመታት ትንቢት ተናገሩ።” በዚያ ጊዜ እንዲህ ይሆናል፤ “ጎግ የእስራኤልን ምድር ሲወጋ፣ ብርቱ ቍጣዬ ይነሣሣል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። በዚያ ጊዜ በቅናቴና በሚያስፈራው ቍጣዬ በእስራኤል ታላቅ የምድር መንቀጥቀጥ ይሆናል ብዬ ተናግሬአለሁ። የባሕር ዓሦች፣ የሰማይ ወፎች፣ የምድር አራዊት፣ በምድር ላይ የሚሳብ ፍጡር ሁሉ፣ እንዲሁም በምድር ላይ ያለ ሰው ሁሉ፣ በፊቴ ይንቀጠቀጣሉ፤ ተራሮች ይገለባበጣሉ፤ ገደሎች ይናዳሉ፤ በተራሮቼም ሁሉ በጎግ ላይ ሰይፍ እጠራለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ የእያንዳንዱም ሰው ሰይፍ በወንድሙ ላይ ያርፋል። በቸነፈርና በደም መፋሰስ እፈርድበታለሁ፤ የዝናብ ዶፍ፣ የበረዶ ድንጋይ፣ የሚያቃጥል ድኝ፣ በርሱና በወታደሮቹ፣ ከርሱም ጋራ ባሉት ሕዝቦች ላይ አወርዳለሁ። በዚህም ታላቅነቴንና ቅድስናዬን አሳያለሁ፤ በብዙ ሕዝቦች ፊት ራሴን አሳውቃለሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” ’