በተማረክን በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፣ በዐሥረኛው ወር፣ በዐምስተኛው ቀን፣ ከኢየሩሳሌም ያመለጠ አንድ ሰው ወደ እኔ መጥቶ፣ “ከተማዪቱ ወደቀች!” አለኝ። ሰውየው ከመድረሱ በፊት በነበረው ምሽት፣ የእግዚአብሔር እጅ በላዬ ላይ ነበረች፤ በማለዳም ሰውየው ወደ እኔ ከመምጣቱ በፊት አፌን ከፈተ፤ አፌም ተከፈተ፤ ከዚያ በኋላ ዝም አላልሁም። ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ በእስራኤል ምድር በፍርስራሾች ውስጥ የሚኖሩት ሕዝቦች፣ ‘አብርሃም አንድ ራሱን ብቻ ነበር፤ ያም ሆኖ ምድሪቱን ወረሰ፤ እኛ ግን ብዙዎች ነን፤ በርግጥ ምድሪቱ ርስት ሆና ተሰጥታናለች’ ይላሉ። ስለዚህ እንዲህ በላቸው፣ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሥጋውን ከነደሙ ትበላላችሁ፤ ዐይኖቻችሁንም ወደ ጣዖቶቻችሁ ታነሣላችሁ፤ ደምም ታፈስሳላችሁ፤ ታዲያ በዚህ ሁኔታ ምድሪቱን ልትወርሱ ታስባላችሁ? በሰይፋችሁ ትመካላችሁ፤ አስጸያፊ ነገሮችን ትፈጽማላችሁ፤ እያንዳንዳችሁም የባልንጀራችሁን ሚስት ታረክሳላችሁ፤ ታዲያ በዚህ ሁኔታ ምድሪቱን ልትወርሱ ይገባችኋል?’ “እንዲህ በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በሕያውነቴ እምላለሁ፤ በፍርስራሾች ውስጥ የተረፉት በሰይፍ ይወድቃሉ፤ በገጠር ያሉትን ቦጫጭቀው እንዲበሏቸው ለዱር አራዊት እሰጣቸዋለሁ፤ በምሽግና በዋሻ ያሉትም በቸነፈር ይሞታሉ። ምድሪቱን ጠፍና ባድማ አደርጋታለሁ፤ የምትመካበት ጕልበቷ እንዳልነበረ ይሆናል፤ የእስራኤልም ተራሮች ማንም እንዳያልፍባቸው ባድማ ይሆናሉ። ካደረጓቸው አስጸያፊ ነገሮች ሁሉ የተነሣ፤ ምድሪቱን ጠፍና ባድማ በማደርግበት ጊዜ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።’ “አንተን በሚመለከት፣ የሰው ልጅ ሆይ፤ የአገርህ ሰዎች በየቤቱ በርና ግድግዳ ሥር ሆነው ስለ አንተ ይነጋገራሉ፤ እርስ በራሳቸውም እንዲህ ይባባላሉ፤ ‘ኑና ከእግዚአብሔር የመጣውን መልእክት እንስማ።’ ሁልጊዜ እንደሚያደርጉት ሕዝቤ ወደ አንተ ይመጣሉ፤ ቃልህንም ለመስማት ከፊትህ ይቀመጣሉ፤ ነገር ግን አይፈጽሙትም። በከንፈራቸው ብዙ ፍቅርን ይገልጣሉ፤ ልባቸው ያረፈው ግን ተገቢ ባልሆነ ጥቅም ላይ ነው። ቃልህን ሰምተው ሥራ ላይ የማያውሉት በመሆናቸው፣ አንተ ለእነርሱ በአማረ ድምፅ የፍቅር ዘፈን የሚዘፍን፣ በዜማ መሣሪያም አሳምሮ የሚጫወት ሙዚቀኛ ሆነህላቸዋል። “ይህ ሁሉ ሲሆን፣ ደግሞም በርግጥ ይሆናል፣ በመካከላቸው ነቢይ እንደ ነበረ፣ ያውቃሉ።”
ሕዝቅኤል 33 ያንብቡ
ያዳምጡ ሕዝቅኤል 33
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሕዝቅኤል 33:21-33
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች