ከሰባቱም ቀን በኋላ፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለእስራኤል ቤት ጕበኛ አድርጌሃለሁ፤ ስለዚህ የምናገረውን ቃል ስማ፤ የምነግርህንም ማስጠንቀቂያ አስተላልፍላቸው። ኀጢአተኛውን ሰው፣ ‘በርግጥ ትሞታለህ’ ባልሁት ጊዜ አንተ ባታስጠነቅቀው፣ ነፍሱንም ያድን ዘንድ ከክፉ ሥራው እንዲመለስ ባትነግረው፣ ያ ኀጢአተኛ በኀጢአቱ ይሞታል፤ አንተን ግን ስለ ደሙ እጠይቅሃለሁ። ነገር ግን ክፉውን ሰው አስጠንቅቀኸው፣ ከኀጢአቱና ከክፉ መንገዱ ባይመለስ፣ እርሱ በኀጢአቱ ይሞታል፤ አንተ ግን ነፍስህን ታድናለህ። “ጻድቁ ሰው ደግሞ ከጽድቁ ተመልሶ ኀጢአት ቢሠራ፣ እኔም መሰናክል በፊቱ ባስቀምጥ እርሱ ይሞታል፤ አንተ አላስጠነቀቅኸውምና በኀጢአቱ ይሞታል፤ ያደረገውም ጽድቅ አይታሰብለትም፤ አንተንም ስለ ደሙ በኀላፊነት እጠይቅሃለሁ። ነገር ግን ጻድቁን ሰው ኀጢአት እንዳይሠራ ብታስጠነቅቀውና እርሱም ኀጢአትን ባይሠራ፣ ተጠንቅቋልና በርግጥ በሕይወት ይኖራል፤ አንተም ነፍስህን ታድናለህ።” የእግዚአብሔር እጅ በላዬ ነበረ፤ እርሱም፣ “ተነሥተህ ወደ ረባዳው ስፍራ ሂድ፤ በዚያ እናገርሃለሁ” አለኝ። እኔም ተነሥቼ ወደ ረባዳው ስፍራ ሄድሁ። በኮቦር ወንዝ አጠገብ ያየሁት ዐይነት ክብር፣ የእግዚአብሔር ክብር በዚያ ቆሞ ነበር፤ እኔም በግንባሬ ተደፋሁ። መንፈስ በውስጤ ገብቶ በእግሬ አቆመኝ፤ እንዲህም ሲል ተናገረኝ፤ “ሂድ፤ ቤትህ ገብተህ በርህን ዝጋ። አንተ፣ የሰው ልጅ ሆይ፤ በገመድ ይጠፍሩሃል፤ ወጥተህም በሕዝብ መካከል እንዳትመላለስ ያስሩሃል። ዐመፀኛ ቤት ቢሆኑም ልትገሥጻቸው እንዳትችል ምላስህን ከላንቃህ ጋራ አጣብቃለሁ፤ ድዳም ትሆናለህ። ነገር ግን በምናገርህ ጊዜ አፍህን እከፍታለሁ፤ አንተም፣ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል’ ትላቸዋለህ። የሚሰማ ይስማ፤ የማይሰማም አይስማ፤ ዐመፀኛ ቤት ናቸውና።
ሕዝቅኤል 3 ያንብቡ
ያዳምጡ ሕዝቅኤል 3
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሕዝቅኤል 3:16-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች