ሕዝቅኤል 3:1-9

ሕዝቅኤል 3:1-9 NASV

እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ በፊትህ ያለውን ብላ፤ ይህን ጥቅልል መጽሐፍ ብላና ሄደህ ለእስራኤል ቤት ተናገር” አለኝ። ስለዚህ አፌን ከፈትሁ፤ እርሱም መጽሐፉን አጐረሠኝ። እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ እኔ የምሰጥህን ይህን ጥቅልል መጽሐፍ ብላ፤ ሆድህንም ሙላ” አለኝ። እኔም በላሁት፤ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠኝ። እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ተነሥተህ ወደ እስራኤል ቤት ሂድ፤ ቃሌንም ንገራቸው። ወደ እስራኤል ቤት እንጂ፣ ንግግሩ ወደማይገባና ቋንቋው ወደማይታወቅ ሕዝብ አልተላክህም፤ ንግግራቸው ወደማይገባና ቋንቋቸው ወደማይታወቅ፣ ቃላቸውንም መረዳት ወደማይቻልህ ብዙ ሕዝብ አልላክሁህም። ወደ እነርሱ ልኬህ ቢሆን ኖሮ፣ በርግጥ ይሰሙህ ነበር። ነገር ግን የእስራኤል ቤት ሁሉ ልበ ደንዳኖችና እልኸኞች ስለ ሆኑ ሊሰሙኝ አልፈለጉም፤ ስለዚህ የእስራኤል ቤት አንተንም አይሰሙህም። እነሆ እኔ በእነርሱ ፊት የማትበገር ጠንካራ አደርግሃለሁ። ግንባርህን ከባልጩት ይልቅ እንደሚጠነክር አልማዝ አደርገዋለሁ። ዐመፀኛ ቤት ቢሆኑም እንኳ አትፍራቸው፤ በፊታቸውም አትሸበር።”