ሕዝቅኤል 29:1-21

ሕዝቅኤል 29:1-21 NASV

በዐሥረኛው ዓመት፣ በዐሥረኛው ወር፣ በዐሥራ ሁለተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ ግብጽ ንጉሥ ወደ ፈርዖን አዙር፤ በርሱና በግብጽ ሁሉ ላይ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም ብለህ ተናገረው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። “ ‘በወንዞችህ መካከል የምትተኛ አንተ ታላቅ አውሬ፣ የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን፤ በአንተ ላይ ተነሥቻለሁ። “የአባይ ወንዝ የእኔ ነው፤ ለራሴም ሠርቼዋለሁ” ትላለህ። ነገር ግን በመንጋጋህ መንጠቆ አስገባለሁ፤ የወንዞችህን ዓሦች ከቅርፊትህ ጋራ አጣብቃለሁ፤ ቅርፊትህ ላይ ከተጣበቁት ዓሦች ሁሉ ጋራ፣ ከወንዞችህ ጐትቼ አወጣሃለሁ። አንተንና በወንዞችህ ያለውን ዓሣ ሁሉ፣ በምድረ በዳ እጥላለሁ። በገላጣ መሬት ላይ ትወድቃለህ፤ የሚሰበስብህ፣ የሚያነሣህም አይኖርም። ለምድር አራዊትና ለሰማይ ወፎች፣ ምግብ እንድትሆን አሳልፌ እሰጥሃለሁ። ከዚያም በግብጽ የሚኖሩ ሁሉ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። “ ‘ለእስራኤል ቤት የሸንበቆ በትር ነበርህ፤ በእጃቸው ሲይዙህ ተሰንጥረህ ትከሻቸውን ወጋህ፤ ሲደገፉህም ተሰብረህ ጀርባቸውን አጐበጥህ። “ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሰይፍ አመጣብሃለሁ፤ ሰዎችህንና እንስሶቻቸውን እገድላለሁ። ግብጽ ባድማና ምድረ በዳ ትሆናለች፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። “ ‘ “የአባይ ወንዝ የእኔ ነው፤ እኔም ሠርቼዋለሁ” ብለሃልና፤ ስለዚህ በአንተ ላይ ተነሥቻለሁ፤ በወንዞችህ ላይ ተነሥቻለሁ፤ የግብጽንም ምድር ከሚግዶል እስከ አስዋን ከዚያም እስከ ኢትዮጵያ ወሰን ድረስ ፍርስራሽና ባድማ አደርጋታለሁ። የሰው እግርም ሆነ የእንስሳ ኰቴ በውስጧ አያልፍም፤ እስከ አርባ ዓመት ማንም አይኖርባትም። የግብጽን ምድር ከጠፉት ምድሮች መካከል እንደ አንዱ ባድማ አደርጋታለሁ፤ ከተሞቿም በፈራረሱት ከተሞች መካከል አርባ ዓመት ባድማ ይሆናሉ፤ ግብጻውያንንም በአሕዛብ መካከል እበትናቸዋለሁ፤ በአገሮችም መካከል እዘራቸዋለሁ። “ ‘ያም ሆኖ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ከአርባ ዓመት በኋላ ግብጻውያንን ከተበተኑበት አገሮች መካከል እሰበስባቸዋለሁ። ከተማረኩበት አመጣቸዋለሁ፤ ወደ አባቶቻቸው ምድር ወደ ጳትሮስ እመልሳቸዋለሁ። ከመንግሥታት ሁሉ አነስተኛ ትሆናለች፤ ከሌሎችም አሕዛብ በላይ ራሷን ከፍ ማድረግ አትችልም። እጅግ ደካማ አደርጋታለሁ፤ ስለዚህ ሌሎችን አሕዛብ እንደ ገና መግዛት አትችልም። ግብጽ ከእንግዲህ ለእስራኤል ሕዝብ መታመኛ አትሆንም፤ ለርዳታ ወደ እርሷ ዘወር ባሉ ጊዜ ላደረጉት ኀጢአት ግን መታሰቢያ ትሆናለች። ከዚያም እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።’ ” በሃያ ሰባተኛው ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር አስቸጋሪ በሆነ ዘመቻ ሰራዊቱን በጢሮስ ላይ አንቀሳቀሰ፤ የሁሉም ራስ ተመልጧል፤ የሁሉም ትከሻ ተልጧል፤ ይሁን እንጂ እርሱና ሰራዊቱ በጢሮስ ላይ ካደረጉት ዘመቻ ያተረፉት ነገር የለም። ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ግብጽን ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እሰጣለሁ፤ ሀብቷን ሁሉ ያግዛል፤ ለሰራዊቱም ደመወዝ ይሆን ዘንድ ምድሪቱን ይበዘብዛል፤ ይመዘብራልም። እርሱና ሰራዊቱ ለእኔ በመልፋታቸው፣ ግብጽን ለድካሙ ዋጋ ሰጥቼዋለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። “በዚያ ቀን ለእስራኤል ቤት ቀንድ አበቅላለሁ፤ በመካከላቸውም አፍህን እከፍታለሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።”