ሕዝቅኤል 28:1-10

ሕዝቅኤል 28:1-10 NASV

ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለጢሮስ ገዥ እንዲህ በለው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘ልብህ በትዕቢት ተወጥሮ፣ “እኔ አምላክ ነኝ፤ በአምላክ ዙፋን ላይ፣ በባሕሮችም ልብ ተቀምጫለሁ” አልህ። ምንም እንኳ እንደ አምላክ ጠቢብ ነኝ ብለህ ብታስብም፣ አንተ ሰው እንጂ አምላክ አይደለህም። ከዳንኤል ይልቅ ጠቢብ ነህን? ከአንተስ የተሰወረ ምስጢር የለምን? በጥበብህና በማስተዋልህ፣ የራስህን ሀብት አከማቸህ፤ ወርቅም ብርም፣ በግምጃ ቤትህ አጠራቀምህ። በንግድ ሥራ እጅግ ከመራቀቅህ የተነሣ፣ በሀብት ላይ ሀብት አካበትህ፤ ከሀብትህ ብዛት የተነሣም፤ ልብህ በትዕቢት ተወጠረ። “ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘እንደ አምላክ ጥበበኛ ነኝ፤ ብለህ ስለምታስብ፣ ከአሕዛብ መካከል እጅግ ጨካኞች የሆኑትን ባዕዳን፣ በአንተ ላይ አመጣለሁ፤ በጥበብህ ውበት ላይ ሰይፋቸውን ይመዝዛሉ፤ ታላቅ ክብርህንም ያረክሳሉ። ወደ ጕድጓድ ያወርዱሃል፤ በጥልቁም ባሕር ውስጥ፣ በባሕሮችም ልብ ውስጥ አስከፊ ሞት ትሞታለህ። ታዲያ በገዳዮችህ ፊት፣ “አምላክ ነኝ” ትላለህን? በገዳዮችህ እጅ ስትገባ፣ አንተ ሰው እንጂ አምላክ አይደለህም። በባዕዳን እጅ፣ ያልተገረዙትን ሰዎች አሟሟት ትሞታለህ፤ እኔ ተናግሬአለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”