የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ አትፈርድባትምን? ደም በምታፈስሰው በዚህች ከተማ ላይ አትፈርድባትምን? ጸያፍ ተግባሯን ፊት ለፊት ንገራት፤ እንዲህም በላት፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በመካከልሽ ደምን በማፍሰስና ጣዖታትን በመሥራት ራስሽን የምታረክሺ፣ ፍርድንም በራስሽ ላይ የምታፈጥኚ ከተማ ሆይ፤ ባፈሰስሽው ደም በድለሻል፤ በሠራሽውም ጣዖት ረክሰሻል፤ ከዚህም የተነሣ ቀንሽን አቅርበሻል፤ ዕድሜሽንም አሳጥረሻል። ስለዚህ ለአሕዛብ መዘባበቻ፣ ለአገሩም ሁሉ መሣለቂያ አደርግሻለሁ። አንቺ የተዋረድሽና ሽብር የሞላብሽ ሆይ፤ በቅርብም በሩቅም ያሉ ይሣለቁብሻል። “ ‘እነሆ በመካከልሽ ያለ እያንዳንዱ የእስራኤል መስፍን ደም ለማፍሰስ ሥልጣኑን ይጠቀማል። አባቶችና እናቶች በውስጥሽ ተዋረዱ፤ መጻተኞች ተጨቈኑ፤ ድኻ አደጎችና መበለቶች ተንገላቱ። ንዋያተ ቅድሳቴን አቃለልሽ፤ ሰንበታቴንም አረከስሽ። ደምን ለማፍሰስ ወሬ የሚያቀብሉ በውስጥሽ አሉ፤ በኰረብታ ቤተ ጣዖት የተሠዋውን የሚበሉና ዝሙትን የሚፈጽሙ ሰዎች በመካከልሽ ይገኛሉ። የአባታቸውን መኝታ የሚደፍሩ ሰዎች በውስጥሽ አሉ፤ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ ባልሆኑበት በወር አበባቸው ጊዜ ሴቶችን በማስገደድ የሚደፍሩ በመካከልሽ ይገኛሉ። በውስጥሽ አንዱ የባልንጀራውን ሚስት ያባልጋል፤ ሌላውም የልጁን ሚስት ያስነውራል፤ ሌላው ደግሞ የገዛ እኅቱ የሆነችውን የአባቱን ልጅ ይደፍራል። በመካከልሽ ያሉ ሰዎች ደም ለማፍሰስ ጕቦ ይቀበላሉ፤ አንቺም ዐራጣና ከፍተኛ ወለድ በመውሰድ ከባልንጀራሽ የማይገባ ትርፍ ዘረፍሽ፤ እኔንም ረስተሻል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። “ ‘ያለ አግባብ ባገኘሽው ጥቅምና በመካከልሽ ባፈሰስሽው ደም ላይ እጄን አጨበጭባለሁ። እኔ ልቀጣሽ በምነሣበት ጊዜ፣ በልበ ሙሉነት መቆም ትችያለሽን? ወይስ እጅሽ ሊበረታ ይችላልን? እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ፤ አደርገዋለሁም። በሕዝቦች መካከል እበትንሻለሁ፤ በየአገሩም እዘራሻለሁ፤ ከርኩሰትሽም አጠራሻለሁ። በሕዝቦች ዘንድ በምትረክሺበት ጊዜ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ።’ ” ከዚያም የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ የእስራኤል ቤት የብረት ዝቃጭ ሆነብኝ፤ ሁሉም በከውር ውስጥ ቀልጦ እንደሚቀር መዳብ፣ ቈርቈሮ፣ ብረትና እርሳስ ናቸው፤ እነዚህ ከብር የሚወጡ ዝቃጭ ናቸው። ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ ‘ሁላችሁም የብረት ዝቃጭ ስለ ሆናችሁ ወደ ኢየሩሳሌም እሰበስባችኋለሁ። ሰው ብርንና መዳብን፣ ብረትንና እርሳስን እንዲሁም ቈርቈሮን ለማቅለጥ በከውር ውስጥ አስገብቶ እሳት እንደሚያነድድበት፣ እኔም እንደዚሁ በቍጣዬና በመዓቴ ወደ ከተማዪቱ እሰበስባችኋለሁ፤ በዚያም አቀልጣችኋለሁ። ሰብስቤአችሁ የቍጣዬን እሳት በእስትንፋሴ አነድድባችኋለሁ፤ እናንተም በዚያ ውስጥ ቀልጣችሁ ትቀራላችሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ቍጣዬን በላያችሁ እንዳፈሰስሁ ታውቃላችሁ። ብር በከውር ውስጥ እንደሚቀልጥ፣ እናንተም በከተማዪቱ ውስጥ ትቀልጣላችሁ፤ በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር ቍጣዬን በላያችሁ እንዳፈሰስሁ ታውቃላችሁ።’ ” ከዚያም የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ምድሪቱን፣ ‘አንቺ ያልነጻሽ በቍጣም ቀን ዝናብ ያላገኘሽ ምድር ነሽ’ በላት። መሳፍንቷ እያገሣ ግዳዩን እንደሚቦጫጭቅ አንበሳ በውስጧ ያሤራሉ፤ ሕዝቡን ይበላሉ፤ ንብረትንና የከበሩ ነገሮችን ይነጥቃሉ፤ ብዙዎችንም ሴቶች መበለት ያደርጋሉ። ካህናቷ በሕጌ ላይ ያምፃሉ፤ ንዋያተ ቅድሳቴን ያረክሳሉ፤ የተቀደሰውን ከረከሰው አይለዩም፤ በጐደፈውና በንጹሑ መካከል ልዩነት እንደሌለ ያስተምራሉ፤ ሰንበታቴን ከማክበር ዘወር ብለዋል፤ በዚህም በመካከላቸው ተንቄአለሁ። በውስጧ የሚገኙ መኳንንቷ ግዳይ እንደሚቦጫጭቁ ተኵላዎች ናቸው፤ በግፍ ትርፍ ለመሰብሰብ ደም ያፈስሳሉ፤ ሕይወትም ያጠፋሉ። ነቢያቷም በሐሰት ራእይና በውሸት ሟርት ይህን ሁሉ ድርጊት ያድበሰብሱላቸዋል፤ እግዚአብሔርም ሳይናገር፣ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል’ ይላሉ። በምድሪቱ የሚኖረው ሕዝብ ይቀማል፤ ይዘርፋል፤ ፍትሕ በማጕደልም ድኻውንና ችግረኛውን ይጨቍናል፤ መጻተኛውንም ይበድላል። “ምድሪቱን እንዳላጠፋት ቅጥሩን የሚጠግን፣ በፈረሰውም በኩል በፊቴ የሚቆምላት ሰው ከመካከላቸው ፈለግሁ፤ ነገር ግን አንድም አላገኘሁም። ስለዚህ መዓቴን አፈስስባቸዋለሁ፤ በጽኑ ቍጣዬም አነድዳቸዋለሁ፤ ያደረጉትንም በራሳቸው ላይ እመልሳለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”
ሕዝቅኤል 22 ያንብቡ
ያዳምጡ ሕዝቅኤል 22
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሕዝቅኤል 22:1-31
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች