ሕዝቅኤል 18:21-32

ሕዝቅኤል 18:21-32 NASV

“ኀጢአተኛ ከሠራው ኀጢአት ሁሉ ተመልሶ ሥርዐቴን ሁሉ ቢጠብቅ፣ ቀናውንና ትክክለኛውን ነገር ቢያደርግ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም። በደሉ ሁሉ አይታሰብበትም፤ በጽድቅ መንገድ ሄዷልና በሕይወት ይኖራል። በውኑ ኀጢአተኛ ሲሞት ደስ ይለኛልን? ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ይልቁን ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ሲኖር ደስ አይለኝምን? “ጻድቅ ሰው ግን ከጽድቁ ተመልሶ ኀጢአት ቢሠራ፣ ኀጢአተኛው የሚያደርገውንም አስጸያፊ ነገር ቢፈጽም፤ ይህ ሰው በውኑ በሕይወት ይኖራልን? ከሠራው ጽድቅ አንዱም አይታሰብለትም፤ ታማኝነቱን በማጕደሉና ከፈጸመው ኀጢአት የተነሣ ይሞታል። “እናንተ ግን፣ ‘የጌታ መንገድ ቀና አይደለችም’ ትላላችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ስማ፤ መንገዴ ቀና አይደለችምን? ቀና ያልሆነውስ የእናንተ መንገድ አይደለምን? ጻድቅ ከጽድቁ ተመልሶ ክፉ ቢሠራ በክፋቱ ይሞታል፤ ከፈጸመውም በደል የተነሣ በሕይወት አይኖርም። ክፉም ሰው ግን ከክፉ ሥራው ተመልሶ ቀናውንና ትክክለኛውን ቢያደርግ ሕይወቱን ያድናል። የፈጸመውን በደል ሁሉ ተገንዝቦ ካደረገው ክፋት ሁሉ ስለ ተመለሰ፣ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም። የእስራኤል ቤት ግን፣ ‘የጌታ መንገድ ቀና አይደለችም’ ይላል። የእስራኤል ቤት ሆይ፤ መንገዴ ቀና አይደለችምን? ቀና ያልሆነችውስ የእናንተ መንገድ አይደለችምን? “የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ስለዚህ እንደየሥራችሁ በእያንዳንዳችሁ ላይ እፈርዳለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እንግዲህ ንስሓ ግቡ፤ በኀጢአት እንዳትጠፉ፣ ከኀጢአታችሁ ሁሉ ተመለሱ። በእኔ ላይ የፈጸማችሁትን በደል ሁሉ ወደ ኋላ ጣሉት፤ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስ ይኑራችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ለምን ትሞታላችሁ? ማንም እንዲሞት አልሻምና፣ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ወደ እኔ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ!