ዘፀአት 9:1-35

ዘፀአት 9:1-35 NASV

ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ወደ ፈርዖን ሂድና እንዲህ በለው፤ ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ “ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።” አሁንም እንዳይሄዱ ብታደርግና ብትከለክላቸው፣ የእግዚአብሔር እጅ በመስክ ላይ ባሉት እንስሳት፣ በፈረሶችህና በአህዮችህ፣ በግመሎችህና በቀንድ ከብቶችህ፣ በበጎችህና በፍየሎችህ ላይ አስከፊ መቅሠፍት ያመጣብሃል። ነገር ግን እግዚአብሔር በእስራኤልና በግብጽ እንስሳት መካከል ልዩነት ያደርጋል፤ ይኸውም የእስራኤል የሆነ ማንኛውም እንስሳ እንዳይሞት ነው።’ ” እግዚአብሔር ጊዜን ወስኖ፣ እንዲህ አለ፤ “በነገው ዕለት እግዚአብሔር በምድሪቱ ላይ ይህን ያደርጋል።” በማግስቱም እግዚአብሔር ነገሩን ፈጸመው፤ የግብጻውያን እንስሳት በሙሉ ዐለቁ፤ ነገር ግን የእስራኤላውያን ከሆኑት እንስሳት አንድም አልሞተም። ፈርዖን ያጣሩ ዘንድ ሰዎች ልኮ ከእስራኤላውያኑ እንስሳት አንድም እንኳ አለመሞቱን ተገነዘበ። ያም ሆኖ ልቡ እንደ ደነደነ ስለ ነበር፣ ሕዝቡን አልለቀቀም። ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን አላቸው፤ “ከምድጃው ዕፍኝ ዐመድ ወስዳችሁ፣ ሙሴ በፈርዖን ፊት ወደ ሰማይ ይበትነው። በግብጽ ምድር ሁሉ ትቢያ ይሆናል፤ በምድሪቱ ሁሉ በሚገኙት ሰዎችና እንስሳት ላይ መግል የያዘ ዕባጭ ይወጣል።” ስለዚህ ከምድጃው ዐመድ ወስደው በፈርዖን ፊት ቆሙ፤ ሙሴም ወደ ሰማይ በተነው፤ መግል የያዘ ዕባጭም በሰዎችና በእንስሳት ላይ ወጣ። በእነርሱና በግብጻውያን ሁሉ ላይ ዕባጭ ወጥቶ ስለ ነበር፣ አስማተኞቹ በሙሴ ፊት መቆም አልቻሉም። እግዚአብሔር ግን የፈርዖንን ልብ አደነደነ፤ እግዚአብሔር ለሙሴ እንደ ተናገረውም፣ ሙሴንና አሮንን መስማት አልፈለገም። ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ማልደህ በጧት ተነሣ፤ ከፈርዖን ፊት ቀርበህ እንዲህ በለው፤ የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ‘ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ፤ አለዚያ በአንተ በሹማምትህና በሕዝብህ ላይ የመቅሠፍቴን መዓት ሁሉ አሁን አወርድብሃለሁ፤ ይኸውም በምድር ሁሉ እንደ እኔ ያለ ማንም እንደሌለ ታውቅ ዘንድ ነው። አሁን እጄን ዘርግቼ አንተንና ሕዝብህን ከገጸ ምድር ሊያጠፋችሁ በሚችል መቅሠፍት በመታኋችሁ ነበር። ነገር ግን ኀይሌን እንዳሳይህና ስሜም በምድር ሁሉ እንዲታወቅ ለዚህ አስነሣሁህ። እስካሁንም በሕዝቤ ላይ እንደ ተነሣህ ነው፤ ይሄዱም ዘንድ አትለቅቃቸውም። ስለዚህ ነገ በዚህ ጊዜ ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በግብጽ ላይ ወርዶ የማያውቅ አስከፊ የበረዶ ማዕበል እልካለሁ። ከብቶችህና በመስክ ላይ ያለህ ማንኛውም ነገር ወደ መጠለያ ይገቡ ዘንድ አሁን ትእዛዝ ስጥ፤ ምክንያቱም በረዶው ወደ መጠለያ ባልገቡትና በመስክ ላይ በቀሩት በማንኛውም ሰውና እንስሳት ላይ ወርዶባቸው ስለሚሞቱ ነው።’ ” የእግዚአብሔርን ቃል የፈሩት የፈርዖን ሹማምት፣ ባሮቻቸውንና ከብቶቻቸውን ለማስገባት ተጣደፉ። የእግዚአብሔርን ቃል ችላ ያሉት ግን ባሮቻቸውንና ከብቶቻቸውን በመስክ ላይ እንደ ነበሩ ተዉአቸው። ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “በመላዪቱ የግብጽ ምድር ባሉት ሰዎች፣ በእንስሳት እንዲሁም በምድሪቱ ላይ በሚበቅሉት ነገሮች ሁሉ ላይ በረዶ እንዲወርድ እጅህን ወደ ሰማይ አንሣ” አለው። ሙሴ በትሩን ወደ ሰማይ ባነሣ ጊዜ እግዚአብሔር ነጐድጓድና በረዶ አወረደ፤ መብረቅም በምድሪቱ ላይ ሆነ። እግዚአብሔር በግብጽ ምድር በረዶ አዘነበ፤ በረዶ ወረደ፤ መብረቅም አብረቀረቀ፤ ግብጽ አገር ከሆነችበት ዘመን አንሥቶ በምድሪቱ ሁሉ እንደዚህ ያለ አስከፊ ማዕበል ሆኖ አያውቅም። በመላው ግብጽ በረዶ በመስክ ላይ ያለውን ሁሉ፣ ሰዎችንና እንስሳትንም መታ፤ በመስክ ላይ የበቀለውን ሁሉ አጠፋ፤ ዛፉን ሁሉ ባዶ አስቀረ። በረዶ ያልወረደበት ቢኖር እስራኤላውያን የሚኖሩበት የጌሤም ምድር ብቻ ነበር። ከዚያም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን አስጠራ፤ እንዲህም አላቸው፤ “አሁንስ በድያለሁ፤ እግዚአብሔር ትክክል ነው፤ እኔና ሕዝቤ ግን ስተናል። መብረቅና በረዶ በዝቶብናልና ወደ እግዚአብሔር ጸልዩልን፤ እንድትሄዱ እለቃችኋለሁ፤ ከዚህ በኋላ በዚህ የመኖር ግዴታ የለባችሁም።” ሙሴም መልሶ፣ “ከከተማዋ በወጣሁ ጊዜ፣ እጆቼን ለጸሎት ወደ እግዚአብሔር እዘረጋለሁ፤ አንተም ምድር የእግዚአብሔር እንደ ሆነች ታውቅ ዘንድ መብረቁ ያቆማል፤ ከእንግዲህ በኋላ በረዶ አይኖርም። ሆኖም አንተና ሹማምትህ አሁንም ቢሆን እግዚአብሔር አምላክን እንደማትፈሩ ዐውቃለሁ።” ተልባው አብቦ፣ ገብሱም ፍሬ ይዞ ስለ ነበር፣ ተልባውና ገብሱ ከጥቅም ውጭ ሆኑ። ስንዴውና አጃው ግን በዚያ ወቅት ባለማፍራቱ አልጠፋም ነበር። ከዚያም ሙሴ ከፈርዖን ተለይቶ ከከተማው ወጣ። እጁን ወደ እግዚአብሔር ዘረጋ፤ ነጐድጓዱና በረዶው ቆመ፤ ዝናቡም በምድሪቱ ላይ መዝነቡን አቆመ። ፈርዖንም ዝናቡ፣ በረዶውና ነጐድጓዱ መቆሙን ባየ ጊዜ እንደ ገና በደለ፤ እርሱና ሹማምቱ ልባቸውን አደነደኑ። ስለዚህ የፈርዖን ልብ ደነደነ፤ እግዚአብሔር ለሙሴ እንደ ተናገረውም እስራኤላውያን ይሄዱ ዘንድ አልለቀቃቸውም።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}