እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ልብ በል፤ እኔ አንተን ለፈርዖን እንደ አምላክ አድርጌሃለሁ፤ ወንድምህ አሮንም ያንተ ነቢይ ይሆናል። እኔ የማዝህን ሁሉ ትናገራለህ፤ ወንድምህ አሮንም እስራኤላውያንን ከአገሩ እንዲወጡ ይለቅቃቸው ዘንድ ለፈርዖን ይነግረዋል። እኔ ግን የፈርዖንን ልብ አደነድናለሁ፤ ታምራዊ ምልክቶችንና ድንቆችን በግብጽ ላይ በብዛት ባደርግም እንኳ፣ አይሰማችሁም። ከዚያም እጄን በግብጽ ላይ አደርጋለሁ፤ በኀያል ፍርድም ሰራዊቴን፣ ሕዝቤን እስራኤላውያንን አወጣለሁ። እጄን በግብጽ ላይ ስዘረጋና እስራኤላውያንንም ከዚያ ሳወጣ፣ ግብጻውያን እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ።” ሙሴና አሮን እግዚአብሔር እንደ አዘዛቸው አደረጉ። ፈርዖንን ባነጋገሩበት ጊዜ ሙሴ ዕድሜው ሰማንያ ዓመት፣ አሮን ደግሞ ሰማንያ ሦስት ነበር። እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፣ “ፈርዖን፣ ‘ታምር አሳዩኝ’ ባላችሁ ጊዜ፣ አሮንን እንዲህ በለው፤ ‘በትርህን ውሰድና በፈርዖን ፊት ጣላት፤’ ከዚያም እባብ ትሆናለች።” ስለዚህ ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ሄደው እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው አደረጉ። አሮን በትሩን በፈርዖንና በሹማምቱ ፊት ጣላት፤ እባብም ሆነች። ከዚያም ፈርዖን ጠቢባኑንና መተተኞቹን ጠራ፤ የግብጽ አስማተኞችም በድብቅ ጥበባቸው ያንኑ አደረጉ፤ እያንዳንዱ የያዛትን በትር ጣለ፤ እባብም ሆነች። ነገር ግን የአሮን በትር የእነርሱን በትሮች ዋጠች። ሆኖም የፈርዖን ልብ ደነደነ፤ እግዚአብሔር ተናግሮ እንደ ነበረውም አላደመጣቸውም። ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “የፈርዖን ልብ ደነደነ፤ ሕዝቡን ለመልቀቅ አልፈቀደም። ወደ ውሃው በሚሄድበት ጊዜ ማልደህ ወደ ፈርዖን ሂድ፤ እንድታገኘውም በአባይ ዳር ተጠባበቅ፤ ወደ እባብ ተለውጣ የነበረችውንም በትር በእጅህ ያዝ። ከዚያም እንዲህ በለው፤ ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር “ሕዝቤ በምድረ በዳ ያመልኩኝ ዘንድ እንዲሄዱ ልቀቃቸው” ብዬ እንድነግርህ ላከኝ፤ አንተ ግን እስካሁን ድረስ ዕሺ አላልህም። እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ “እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ በዚህ ታውቃለህ፤ እይ! በዚህች በእጄ በያዝኋት በትር የአባይን ውሃ እመታለሁ፤ ወደ ደምም ይለወጣል። በአባይ ወንዝ ውስጥ ያለው ዓሣ ይሞታል፤ ወንዙ ይከረፋል፤ ግብጻውያንም ውሃውን መጠጣት አይችሉም።” ’ ” እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ “አሮንን፣ ‘በትርህን ውሰድና በግብጽ ውሆች ላይ፣ ይኸውም በምንጮች፣ በቦዮች፣ በኵሬዎችና በውሃ ማጠራቀሚያዎች ላይ እጅህን ዘርጋ’ ብለህ ንገረው፤ ወደ ደምም ይለወጣሉ። ከዕንጨትና ከድንጋይ በተሠሩ ውሃ መያዣዎች ውስጥም ሳይቀር በግብጽ ምድር ደም በየቦታው ይሆናል።” ሙሴና አሮን እግዚአብሔር እንደ አዘዛቸው አደረጉ። እርሱም በፈርዖንና በሹማምቱ ፊት በትሩን አንሥቶ የአባይን ወንዝ ውሃ መታ፤ ውሃውም በሙሉ ወደ ደም ተለወጠ። በአባይ ያሉት ዓሦች ሞቱ፤ ወንዙም ከመከርፋቱ የተነሣ ግብጻውያኑ ውሃውን ሊጠጡት አልቻሉም። በግብጽ ምድር ሁሉ ደም ነበረ። የግብጽ አስማተኞች በድብቅ ጥበባቸው ተመሳሳይ ነገር አደረጉ፤ የፈርዖንም ልብ ደነደነ፤ ልክ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው ሙሴንና አሮንን አልሰማቸውም። ተመልሶ ወደ ቤተ መንግሥቱ ገባ እንጂ ይህን ከቁም ነገር አልቈጠረውም። ግብጻውያን ሁሉ የወንዙን ውሃ መጠጣት ባለመቻላቸው ውሃ ለማግኘት የአባይን ዳር ይዘው ጕድጓድ ቈፈሩ። እግዚአብሔር አባይን ከመታ ሰባት ቀን ሞላ።
ዘፀአት 7 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፀአት 7
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፀአት 7:1-25
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች