ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ “ማደሪያውን ይኸውም የመገናኛውን ድንኳን በወሩ የመጀመሪያ ቀን ትከለው፤ የምስክሩን ታቦት በውስጡ አኑር፤ ታቦቱንም በመጋረጃው ጋርደው። ጠረጴዛውንም ወደ ውስጥ አምጥተህ ዕቃዎቹን በላዩ ላይ አሰናዳ፤ ከዚያም መቅረዙን አስገብተህ መብራቶቹን በቦታቸው አስቀምጥ። የዕጣኑን የወርቅ መሠዊያ በምስክሩ ታቦት ፊት ለፊት አስቀምጠው፤ ከማደሪያውም መግቢያ ላይ መጋረጃውን አድርግ። “የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውን በማደሪያው መግቢያ ፊት ለፊት፣ በመገናኛው ድንኳን አስቀምጠው። የመታጠቢያውን ሰን በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አኑርበት፤ ውሃም አኑርበት። በዙሪያውም የአደባባዩን ቅጥር ትከል፤ መጋረጃውንም በአደባባዩ መግቢያ ላይ አድርገው። “ቅብዐ ዘይቱን ወስደህ ማደሪያውንና በውስጡ ያለውን ሁሉ ቅባ፤ እርሱንና ዕቃውን ሁሉ ቀድስ፤ የተቀደሰም ይሆናል። ከዚያም የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውንና ዕቃዎቹን ሁሉ ቅባ፤ መሠዊያውን ቀድስ፣ እጅግም የተቀደሰ ይሆናል። የመታጠቢያው ሰንና ማስቀመጫውን ቅባ፤ ቀድሳቸውም። “አሮንና ወንዶች ልጆቹን ወደ መገናኛው ድንኳን መግቢያ አምጥተህ በውሃ ዕጠባቸው። ከዚያም አሮንን የተቀደሰውን ልብስ አልብሰው፤ ካህን ሆኖ ያገለግለኝ ዘንድ ቅባው፤ ቀድሰውም። ወንዶች ልጆቹን አምጥተህ ሸሚዝ አልብሳቸው። ካህናት ሆነው ያገለግሉኝ ዘንድ ልክ አባታቸውን እንደ ቀባህ ቅባቸው፤ መቀባታቸውም በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ለሚቀጥል ክህነት ነው።” ሙሴ ሁሉንም ነገር ልክ እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ።
ዘፀአት 40 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፀአት 40
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፀአት 40:1-16
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች