እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ “እንደ መጀመሪያዎቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላት ጥረብ፤ እኔም አንተ በሰበርሃቸው በመጀመሪያዎቹ ጽላት ላይ የነበሩትን ቃሎች እጽፍባቸዋለሁ። በማለዳ ተዘጋጅተህ ወደ ሲና ተራራ ውጣ፤ በዚያ በተራራው ጫፍ ላይ በፊቴ ቁም፤ ከአንተ ጋራ ማንም እንዳይመጣ ወይም በተራራው ላይ በየትኛውም ቦታ እንዳይታይ፤ የበግና የፍየል መንጋዎች የቀንድ ከብቶችም እንኳ፣ በተራራው ፊት ለፊት መጋጥ የለባቸውም።” ስለዚህ ሙሴ እንደ መጀመሪያዎቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላት ጠርቦ፣ እግዚአብሔር እንዳዘዘው በማለዳ ወደ ሲና ተራራ ወጣ፤ ሁለቱን የድንጋይ ጽላትም በእጆቹ ያዘ። ከዚያም እግዚአብሔር በደመና ወረደ፤ በዚያም ከርሱ ጋራ ቆሞ ስሙን እግዚአብሔርን ዐወጀ። እርሱም በሙሴ ፊት እንዲህ እያለ እያወጀ ዐለፈ፤ “እግዚአብሔር ርኅሩኅና ቸር አምላክ፣ እግዚአብሔር ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ፣ ፍቅርን ለሺሕዎች የሚጠብቅ፣ ክፋትን፣ ዐመፅንና ኀጢአትን ይቅር የሚል፣ በደለኛውን ግን ሳይቀጣ ዝም ብሎ አይተውም፤ በአባቶች ኀጢአት ልጆችን የልጅ ልጆቻቸውን እስከ ሦስትና አራት ትውልድ ይቀጣል።” ሙሴም ወዲያውኑ ወደ መሬት ዝቅ ብሎ ሰገደ፤ “አቤቱ ጌታ ሆይ፤ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ፣ ጌታ ከእኛ ጋራ ይሂድ፤ ይህ ዐንገተ ደንዳና ሕዝብ ቢሆንም እንኳ፣ ክፋታችንንና ኀጢአታችንን ይቅር በል፤ እንደ ርስትህም አድርገህ ውሰደን።” ከዚያም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “ከአንተ ጋራ ኪዳን እገባለሁ፤ ከዚህ ቀደም በዓለም ሁሉ ለየትኛውም ሕዝብ ከቶ ያልተደረገ፣ በሕዝብህ ሁሉ ፊት ድንቅ አደርጋለሁ፤ በመካከላቸው ዐብረሃቸው የምትኖር ሕዝብ እኔ እግዚአብሔር ለአንተ የማደርግልህ ሥራ የቱን ያህል አስፈሪ እንደ ሆነ ያያሉ። ዛሬ የማዝዝህን ፈጽም፤ አሞራውያንን፣ ከነዓናውያንን፣ ኬጢያውያንን፣ ፌርዛውያንን፣ ኤዊያውያንንና ኢያቡሳውያንን በፊትህ አስወጣቸዋለሁ። ከምትሄድበት አገር ነዋሪዎች ጋራ ቃል ኪዳን እንዳታደርግ ተጠንቀቅ፤ አለዚያ በመካከልህ ወጥመድ ይሆኑብሃል። መሠዊያዎቻቸውን ሰባብሩ፤ የማምለኪያ ዐምዶቻቸውን አድቅቁ፤ የአሼራ ዐጸዶቻቸውንም ቍረጡ። ስሙ ቀናተኛ የሆነው እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ ነውና ሌላ አምላክ አታምልክ። “በምድሪቱ ከሚኖሩት ጋራ ቃል ኪዳን እንዳታደርግ ተጠንቀቅ፤ ምክንያቱም አምላኮቻቸውን ተከትለው ባመነዘሩና መሥዋዕትም ባቀረቡላቸው ጊዜ ይጋብዙሃል፤ አንተም መሥዋዕታቸውን ትበላለህ። ለወንዶች ልጆችህም ሴቶች ልጆቻቸውን ስታጭላቸውና እነዚህም ሴቶች ልጆች አምላኮቻቸውን በመከተል ሲያመነዝሩ፣ ወንዶች ልጆችህን ተመሳሳይ ድርጊት እንዲፈጽሙ ያነሣሧቸዋል። “ቀልጠው የሚሠሩ አማልክትን አታብጅ። “የቂጣን በዓል አክብር። እንዳዘዝሁህም ለሰባት ቀን ቂጣ ብላ፤ ይህንም በተወሰነው ጊዜ በአቢብ ወር አድርግ፤ በዚያ ወር ከግብጽ ወጥተሃልና። “የመንጋህ ወይም የበግና የፍየልህ፣ የቀንድ ከብትህ ተባዕት በኵር ሁሉ ሳይቀር፣ ከማሕፀን በኵር ሆኖ የሚወጣ ሁሉ የእኔ ነው። የአህያን በኵር በበግ ጠቦት ዋጀው፤ ካልዋጀኸው ግን ዐንገቱን ስበረው። በኵር ወንድ ልጆችህን ሁሉ ዋጅ። “ማንም በፊቴ ባዶ እጁን አይቅረብ። “ስድስት ቀን ሥራ፤ በሰባተኛው ቀን ግን ዕረፍ፤ በዕርሻና በመከር ወቅት እንኳ ቢሆን ማረፍ አለብህ። “የሰባቱን ሱባዔ የመከር በዓል ከስንዴው መከር በኵራት ጋራ፣ እንዲሁም የመክተቻ በዓልን በዓመቱ መጨረሻ ላይ አክብር። በዓመት ሦስት ጊዜ ወንድ ሁሉ በእስራኤል አምላክ በጌታ እግዚአብሔር ፊት ይቅረብ። አሕዛብን ከፊትህ አስወጣለሁ፤ ድንበርህን አሰፋለሁ፤ በዓመት ሦስት ጊዜ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ለመቅረብ ስትወጣ፣ ምድርህን ማንም አይመኝም። “እርሾ ካለው ከማንኛውም ነገር ጋራ የደም መሥዋዕት ለእኔ አታቅርብ፤ ከፋሲካ በዓል የተረፈው መሥዋዕት እስከ ማለዳ አይቈይ። “የምድርህን ምርጥ ፍሬ በኵራት ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ቤት አምጣ። “ጠቦት ፍየልን በእናቱ ወተት አትቀቅል።” ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “እነዚህን ቃሎች ጻፋቸው፤ በእነዚህ ቃሎች መሠረት ከአንተና ከእስራኤል ጋራ ቃል ኪዳን አድርጌአለሁና” አለው። ሙሴ እህል ሳይበላ፣ ውሃም ሳይጠጣ ከእግዚአብሔር ጋራ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በዚያ ነበር፤ በጽላቱ ላይ የቃል ኪዳኑን ቃሎች፣ ዐሥርቱ ትእዛዛትን ጻፈ።
ዘፀአት 34 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፀአት 34
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፀአት 34:1-28
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች