ሕዝቡ ሙሴ ከተራራው ላይ ሳይወርድ ብዙ እንደ ቈየ ባዩ ጊዜ፣ ወደ አሮን ተሰብስበው፣ “ናና በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን፤ ያ ከግብጽ ያወጣን ሙሴ ምን እንዳገኘው አናውቅም” አሉት። አሮንም፣ “የሚስቶቻችሁን፣ የወንድና የሴት ልጆቻችሁን የጆሮ ወርቅ አውልቃችሁ ወደ እኔ አምጡ” ብሎ መለሰላቸው። ሕዝቡም ሁሉ የጆሮ ወርቃቸውን አውልቀው ወደ አሮን አመጡ። እርሱም የሰጡትን ወስዶ በመሣሪያ በመቅረጽ በጥጃ ምስል ጣዖት አድርጎ ሠራው፤ ከዚያም እነርሱ፣ “እስራኤል ሆይ፤ ከግብጽ ያወጡህ አማልክት እነዚህ ናቸው” አሉ። አሮን ይህን ባየ ጊዜ በወርቅ ጥጃው ፊት ለፊት መሠዊያ ሠርቶ፣ “ነገ ለእግዚአብሔር በዓል ይሆናል” ብሎ ዐወጀ። በማግስቱም ሕዝቡ በማለዳ ተነሥተው የሚቃጠል መሥዋዕት ሠዉ፤ የኅብረት መሥዋዕት አቀረቡ፤ ከዚህም በኋላ ይበሉና ይጠጡ ዘንድ ተቀመጡ፤ ሊዘፍኑም ተነሡ። ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “ከግብጽ ያወጣሃቸው ሕዝብህ ስተዋልና ውረድ” አለው። “ካዘዝኋቸው ፈቀቅ ለማለት ፈጣኖች ሆኑ፤ ለራሳቸውም በጥጃ ምስል የተቀረጸ ጣዖትን ሠሩ፤ ለርሱም ሰገዱለት፤ ሠዉለትም፤ እንዲሁም፣ ‘እስራኤል ሆይ፤ ከግብጽ ምድር ያወጡህ አማልክትህ እነዚህ ናቸው’ አሉ።” እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እነዚህን ሕዝብ አይቻቸዋለሁ፤ ዐንገተ ደንዳናዎችም ናቸው። አሁንም በእነርሱ ላይ፣ ቍጣዬ እንዲነድድና እንዳጠፋቸው ተወኝ፤ ከዚያም አንተን ለታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ።” ነገር ግን ሙሴ የአምላኩን የእግዚአብሔርን ቸርነት ፈለገ፤ እንዲህም አለ፤ “እግዚአብሔር ሆይ በታላቅ ሥልጣንህና በኀያል ክንድህ ከግብጽ ባወጣኸው ሕዝብህ ላይ ቍጣህ ለምን ይነድዳል? ግብጻውያን፣ ‘በተራሮቹ ላይ ሊገድላቸው፣ ከገጸ ምድርም ሊያጠፋቸው ስለ ፈለገ ነው ያወጣቸው’ ለምን ይበሉ? ከክፉ ቍጣህ ተመለስ፤ ታገሥ፤ በሕዝብህም ላይ ጥፋት አታምጣ። ለባሪያዎችህ ለአብርሃም፣ ለይሥሐቅና ለእስራኤል፣ ‘ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛዋለሁ፤ ለዘርህም ተስፋ አድርጌ የሰጠኋቸውን ይህችን ምድር ሁሉ እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘላለምም ርስታቸው ትሆናለች’ በማለት በራስህ የማልኸውን አስታውስ።” ከዚያም እግዚአብሔር ታገሠ፤ በሕዝቡም ላይ አመጣባቸዋለሁ ያለውን ጥፋት አላመጣባቸውም። ሙሴም ሁለቱን የምስክር ጽላት በእጆቹ ይዞ ከተራራው ወረደ፤ ጽላቱም ከፊትና ከኋላ በሁለቱም ጐኖች ተጽፎባቸው ነበር። ጽላቱ የእግዚአብሔር ሥራ ነበሩ፤ በጽላቱ ላይ የተቀረጸ ጽሕፈትም የእግዚአብሔር ጽሕፈት ነበር። ኢያሱ የሕዝቡን የጩኸት ድምፅ በሰማ ጊዜ ሙሴን፣ “በሰፈሩ ውስጥ የጦርነት ድምፅ አለ አለው።” ሙሴም፣ “የድል ድምፅ አይደለም፤ የሽንፈትም ድምፅ አይደለም፤ የምሰማው የዘፈን ድምፅ ነው” ብሎ መለሰለት። ሙሴ ወደ ሰፈሩ ደርሶ ጥጃውንና ጭፈራውን ባየ ጊዜ ቍጣው ነደደ፤ ጽላቱን ከእጁ በመወርወር ከተራራው ግርጌ ሰባበራቸው። ያበጁትን ጥጃ ወስዶ በእሳት አቃጠለው፤ ከዚያም ዱቄት እስኪሆን ፈጨው፤ በውሃ ላይ በተነው፤ እስራኤላውያንም እንዲጠጡት አደረገ። ሙሴም አሮንን፣ “ወደዚህ አስከፊ ኀጢአት ትመራቸው ዘንድ እነዚህ ሕዝብ ምን አደረጉህ?” አለው። አሮንም መልሶ፣ “ጌታዬ ሆይ፤ አትቈጣ” ብሎ መለሰለት፤ “ይህ ሕዝብ ሁልጊዜ ለክፋት ያዘነበለ መሆኑን አንተ ታውቃለህ። እነርሱም ‘በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን፤ ያ ከግብጽ ያወጣን ሙሴ ምን እንዳገኘው አናውቅም’ አሉኝ። ስለዚህ፣ ‘ማንኛውም ዐይነት የወርቅ ጌጣጌጥ ያለው ሁሉ ያውልቀው’ አልኋቸው፤ ከዚያም ወርቁን ሰጡኝ፤ ወደ እሳቱ ጣልሁት፤ ይህም ጥጃ ወጣ።” ሕዝቡ ከቍጥጥር ውጭ እንደ ሆኑ፣ አሮንም መረን እንደ ለቀቃቸውና በጠላቶቻቸውም ዘንድ መሣለቂያ እንደ ሆኑ ሙሴ አስተዋለ። ስለዚህ በሰፈሩ መግቢያ ላይ ቆሞ፣ “የእግዚአብሔር የሆነ ሁሉ ወደ እኔ ይምጣ” አለ፤ ሌዋውያኑም ሁሉ ከርሱ ጋራ ሆኑ። ከዚያም፣ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ‘እያንዳንዱ ሰው በወገቡ ላይ ሰይፍ ይታጠቅ፤ በሰፈር ውስጥ ከዳር እዳር እየተመላለሰ እያንዳንዱ ወንድሙን፣ ጓደኛውንና ጎረቤቱን ይግደል’ ” አላቸው። ሌዋውያኑ ሙሴ እንዳዘዛቸው ፈጸሙ፤ በዚያም ዕለት ከሕዝቡ ሦስት ሺሕ ያህል ዐለቁ። ከዚያም ሙሴ፣ “በራሳችሁ ወንዶች ልጆችና ወንድሞች ላይ በመነሣታችሁ፣ በዛሬዋ ቀን ለእግዚአብሔር የተለያችሁ ሆናችኋል፤ በዛሬዋም ዕለት ባርኳችኋል” አለ። በማግስቱም ሙሴ ሕዝቡን፣ “እጅግ የከፋ ኀጢአት ሠርታችኋል፤ አሁን ግን ወደ እግዚአብሔር እወጣለሁ፤ ምናልባት ኀጢአታችሁን ማስተስረይ እችል ይሆናል” አላቸው። ስለዚህ ሙሴ ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ እንዲህ አለው፤ “ወዮ እነዚህ ሕዝብ የሠሩት ምን ዐይነት የከፋ ኀጢአት ነው! ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት ሠሩ። አሁን ግን አቤቱ ኀጢአታቸውን ይቅር በል፤ አለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍ እኔን ደምስሰኝ።” እግዚአብሔር ለሙሴ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “የበደለኝን ሁሉ ከመጽሐፌ እደመስሰዋለሁ። አሁን ሂድ፤ ሕዝቡን ወደ ተናገርሁት ስፍራ ምራው፤ መልአኬም በፊትህ ይሄዳል፤ ሆኖም የምቀጣበት ጊዜ ሲደርስ፣ ስለ ኀጢአታቸው እቀጣቸዋለሁ።” አሮን በሠራው ጥጃ ባደረጉት ነገር እግዚአብሔር ሕዝቡን በመቅሠፍት መታ።
ዘፀአት 32 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፀአት 32
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፀአት 32:1-35
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች