ዘፀአት 3:1-22

ዘፀአት 3:1-22 NASV

አንድ ቀን ሙሴ የምድያም ካህን የሆነውን የዐማቱን የዮቶር በጎችና ፍየሎች እየጠበቀ ሳለ፣ መንጋውን እየነዳ ወደ ምድረ በዳው ዳርቻ አምርቶ የእግዚአብሔር ተራራ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ኮሬብ ቀረበ። እዚያም የእግዚአብሔር መልአክ በቍጥቋጦው ውስጥ በሚንቀለቀል የእሳት ነበልባል መካከል ተገለጠለት። ሙሴም ቍጥቋጦው በእሳት ቢያያዝም እንኳ፣ አለመቃጠሉን አየ። ሙሴም፣ “ቍጥቋጦው ለምን እንደማይቃጠል ቀረብ ብዬ ይህን አስገራሚ ነገር ልመልከት” አለ። ሙሴ ሁኔታውን ለመመልከት መቅረቡን እግዚአብሔር ባየ ጊዜ፣ ከቍጥቋጦው ውስጥ እግዚአብሔር “ሙሴ፣ ሙሴ” ብሎ ጠራው። ሙሴም “አቤት እነሆኝ” አለው። እግዚአብሔርም፣ “ወደዚህ እንዳትቀርብ፤ ይህች የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች ስለ ሆነች ጫማህን ከእግርህ አውልቅ” አለው። ቀጥሎም፣ “እኔ የአባቶችህ የአብርሃም፣ የይሥሐቅ፣ የያዕቆብ አምላክ ነኝ” አለው። በዚህ ጊዜ ሙሴ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት ማየት ስለ ፈራ ፊቱን ሸፈነ። ከዚያም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፣ “በግብጽ አገር የሚኖሩትን የሕዝቤን መከራ አይቻለሁ፤ ከአሠሪዎቻቸው ጭካኔ የተነሣ የሚያሰሙትንም ጩኸት ሰምቻለሁ፤ ሥቃያቸውንም ተረድቻለሁ። ስለዚህም ከግብጻውያን እጅ ልታደጋቸውና ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ሰፊና ለም ወደሆነችው ወደ ከነዓናውያን፣ ኬጢያውያን፣ አሞራውያን፣ ፌርዛውያን፣ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር ላወጣቸው ወርጃለሁ። አሁንም የእስራኤል ልጆች ጩኸት ወደ እኔ ደርሷል፤ ግብጻውያን የሚያደርሱባቸውን ግፍ አይቻለሁ። በል እንግዲህ ና፤ ሕዝቤን፣ የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ምድር እንድታወጣቸው ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ”። ሙሴ እግዚአብሔርን፣ “ወደ ፈርዖን የምሄድና የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ የማወጣ እኔ ማን ነኝ?” አለው። እግዚአብሔርም፣ “እኔ ከአንተ ጋራ እሆናለሁ፤ እኔ የላክሁህ ለመሆኑ ምልክቱ ይህ ነው፤ ሕዝቡን ከግብጽ ካወጣሃቸው በኋላ በዚህ ተራራ ላይ እግዚአብሔርን ታመልካላችሁ” አለው። ሙሴም እግዚአብሔርን፣ “ወደ እስራኤል ልጆች ሄጄ፣ ‘የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ልኮኛል’ ስላቸው ‘ስሙ ማን ነው?’ ብለው ቢጠይቁኝ ምን እላቸዋለሁ?” አለው። እግዚአብሔርም ሙሴን፣ “እኔ፣ ያለሁና የምኖር ነኝ፤ ስለዚህም ለእስራኤል ልጆች፣ ‘ያለና የሚኖር ልኮኛል’ ብለህ ንገራቸው” አለው። ደግሞም እግዚአብሔርም ሙሴን፣ “ ‘የአባቶቻችሁ የአብርሃም አምላክ፣ የይሥሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ የሆነው እግዚአብሔር ወደ እናንተ ልኮኛል፤’ “ስሜም ለዘለዓለም ይኸው ነው፤ ወደ ፊት በተከታታይ በሚነሣው ትውልድ ሁሉ የምታሰበው በዚህ ስም ነው ብለህ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው” አለው። “ሂድና የእስራኤልን አለቆች ሰብስበህ፣ ‘የአባቶቻችሁ የአብርሃም፣ የይሥሐቅና የያዕቆብ አምላክ የሆነው እግዚአብሔር ተገለጠልኝና እንዲህ አለኝ፤ ጐብኝቻችኋለሁ፤ በግብጽ የደረሰባችሁንም አይቻለሁ። ስለዚህም በግብጽ ከምትቀበሉት መከራ አውጥቼ ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ወደ ከነዓናውያን፣ ወደ ኬጢያውያን፣ ወደ አሞራውያን፣ ወደ ፌርዛውያን፣ ወደ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር አገባችኋለሁ’ ብሏል ብለህ ንገራቸው” አለኝ። “የእስራኤል አለቆችም ይሰሙሃል። አንተና የእስራኤል አለቆች ወደ ግብጽ ንጉሥ ትሄዱና፣ ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር ተገለጠልን፤ ስለዚህም ወደ ምድረ በዳ የሦስት ቀን መንገድ ተጕዘን ለአምላካችን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት እንድናቀርብ ፍቀድልን’ ብላችሁ ትነግሩታላችሁ። የግብጽ ንጉሥ ግን በኀያል ክንድ ካልተገደደ በቀር መቼም እንደማይለቅቃችሁ ዐውቃለሁ። ስለዚህ እኔ እጅግ ድንቅ የሆኑ ታምራትን እዚያው እመካከላቸው በማድረግ ክንዴን ዘርግቼ ግብጻውያንን እመታቸዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ እንድትሄዱ ይለቅቃችኋል። “ይህ ሕዝብ በግብጻውያን ዘንድ የመወደድን ጸጋ እንዲያገኝ ስለማደርግ በምትወጡበት ጊዜ ባዶ እጃችሁን አትሄዱም። እያንዳንዷ ዕብራዊት ከጎረቤቷም ይሁን ዐብራት ከምትኖረው ግብጻዊት የብርና የወርቅ ጌጣጌጦች እንደዚሁም ልብስ እንድትሰጣት ትጠይቅ። እነዚህንም ሁሉ ወስዳችሁ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁን ታስጌጧቸዋላችሁ፤ ታለብሷቸዋላችሁም። በዚህም መንገድ የግብጻውያኑን ሀብት በእጃችሁ አግብታችሁ ትወጣላችሁ።”

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}