ሙሴ ወደ ሕዝቡ ሄዶ የእግዚአብሔርን ቃሎችና ሕጎች ሁሉ በነገራቸው ጊዜ በአንድ ድምፅ ሆነው፣ “እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን” አሉ። ከዚያም ሙሴ እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ ጻፈ። በማግስቱም ማልዶ ተነሥቶ፣ በተራራው ግርጌ መሠዊያን ሠራ፤ ዐሥራ ሁለቱን የእስራኤልን ነገዶች የሚወክሉ ዐሥራ ሁለት የድንጋይ ዐምዶችን አቆመ። ከዚያም ወጣት ወንድ እስራኤላውያንን ላከ፤ እነርሱም የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረቡ፤ ወይፈኖችን የኅብረት መሥዋዕት አድርገው ለእግዚአብሔር ሠዉ። ሙሴ የደሙን እኩሌታ ወስዶ በጐድጓዳ ሳሕኖች አኖረው፤ የቀረውንም እኩሌታ በመሠዊያው ላይ ረጨው። ከዚያም የኪዳኑን መጽሐፍ ወስዶ ለሕዝቡ አነበበላቸው፤ እነርሱም፣ “እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን፤ እንታዘዛለን” አሉ። ከዚያም ሙሴ ደሙን ወሰደ፤ ሕዝቡም ላይ ረጭቶ፣ “ይህ እነዚህን ቃሎች በሰጠ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋራ የገባው የኪዳኑ ደም ይህ ነው” አላቸው። ሙሴና አሮን፣ ናዳብና አብዩድ እንደዚሁም ሰባዎቹ የእስራኤል አለቆች ወደ ተራራው ወጡ፣ የእስራኤልንም አምላክ አዩ፤ ከእግሩም በታች እንደ ብሩህ ሰማይ የጠራ የሰንፔር ወለል ነበር። ሆኖም እግዚአብሔር በእስራኤል ሕዝብ አለቆች ላይ እጁን አላነሣባቸውም። እግዚአብሔርን አዩ፣ በሉ፤ ጠጡም። እግዚአብሔር ሙሴን፣ “በተራራው ላይ ወደ እኔ ና፤ በዚህም ቈይ፤ እኔም መመሪያ እንዲሆናቸው ሕግና ትእዛዞች የጻፍሁባቸውን የድንጋይ ጽላት እሰጥሃለሁ” አለው። ከዚያም ሙሴ ከረዳቱ ከኢያሱ ጋራ ዐብሮ ሄደ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወጣ። እርሱም ሽማግሌዎችን “ወደ እናንተ እስክንመለስ ድረስ በዚህ ቈዩ፤ አሮንና ሖር ከእናንተ ጋራ ናቸው፤ ክርክር ያለው ባለጕዳይ ቢኖር ወደ እነርሱ ይሂድ።” አላቸው። ሙሴ ወደ ተራራ ሲወጣ ደመናው ተራራውን ሸፈነ፤ የእግዚአብሔርም ክብር በሲና ተራራ ላይ ወረደ፤ ደመናውም ተራራውን እስከ ስድስት ቀን ድረስ ሸፈነው፤ በሰባተኛውም ቀን እግዚአብሔር በደመናው ውስጥ ሆኖ ሙሴን ጠራው። ለእስራኤላውያን የእግዚአብሔር ክብር በተራራው ጫፍ ላይ እንደሚባላ እሳት ሆኖ ይታይ ነበር። ከዚያም ሙሴ ወደ ተራራው ሲወጣ ደመናው ውስጥ ገባ፤ በተራራውም ላይ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቈየ።
ዘፀአት 24 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፀአት 24
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፀአት 24:3-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች