ዘፀአት 23:20-31

ዘፀአት 23:20-31 NASV

“እነሆ፤ በጕዞ ላይ ሳለህ የሚጠብቅህንና ወዳዘጋጀሁልህ ስፍራ የሚያስገባህን መልአክ በፊትህ ልኬልሃለሁ። በጥንቃቄ ተከተለው፤ የሚናገረውንም ልብ ብለህ ስማው፤ አታምፅበት። ስሜ በርሱ ላይ ነውና ዐመፅህን ይቅር አይልም። የሚናገረውን በጥንቃቄ ብታደምጥና ያልኩህን ሁሉ ብታደርግ ለጠላቶችህ ጠላት እሆናለሁ፤ የሚቃወሙህን እቃወማለሁ። መልአኬ በፊትህ ይሄዳል፤ አንተንም ወደ አሞራውያን፣ ወደ ኬጢያውያን፣ ወደ ፌርዛውያን፣ ወደ ከነዓናውያን፣ ወደ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር ያስገባሃል፤ እኔም እነርሱን አጠፋቸዋለሁ። ለአማልክታቸው አትስገድ፤ ወይም አታምልካቸው፤ ወይም ልምዳቸውን አትከተል፤ እነርሱን ማፈራረስ አለብህ፤ የአምልኮ ድንጋዮቻቸውንም ሰባብር። አምላክህን እግዚአብሔርን አምልክ፤ በረከቱም በምትበላውና በምትጠጣው ላይ ይሆናል፤ በሽታንም ከአንተ ዘንድ አርቃለሁ። በምድርህም የሚያስወርዳት ወይም መካን ሴት አትኖርም፤ ረዥም ዕድሜም እሰጥሃለሁ። “በሚያጋጥሙህ አሕዛብ ሁሉ ላይ ማስፈራቴን በፊትህ እልካለሁ፤ ግራም አጋባቸዋለሁ፤ ጠላቶችህ ሁሉ ወደ ኋላ ተመልሰው እንዲሸሹ አደርጋለሁ። ኤዊያውያንን፣ ከነዓናውያንን፣ ኬጢያውያንን ከመንገድህ ለማስወጣት ተርብን በፊትህ እሰድዳለሁ። ነገር ግን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አላወጣቸውም፤ ምክንያቱም ምድሪቱ ባድማ ሆና የዱር አራዊት ይበዙባችኋል። ቍጥርህ ጨምሮ ምድሪቱን ለመውረስ እስክትበቃ ድረስ ጥቂት በጥቂት ከፊታችሁ አባርራቸዋለሁ። “ድንበርህን ከቀይ ባሕር እስከ ፍልስጥኤም ባሕር፣ ከምድረ በዳው እስከ ወንዙ ድረስ አደርገዋለሁ፤ በምድሪቱም ላይ የሚኖሩትን ሰዎች አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ አንተም አሳድደህ ከፊትህ ታስወጣቸዋለህ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}