ዘፀአት 23:1-13
ዘፀአት 23:1-13 NASV
“የሐሰት ወሬ አትንዛ፤ ተንኰል ያለበትን ምስክርነት በመስጠት ክፉውን ሰው አታግዝ። “ክፉ በማድረግ ብዙዎችን አትከተል፤ በሕግ ፊት ምስክርነት ስትሰጥ፣ ከብዙዎቹ ጋራ ተባብረህ ፍትሕ አታጣምም። በዳኝነት ጊዜ ለድኻው አታድላ። “የጠላትህ በሬ ወይም አህያ ሲባዝን ብታገኘው ወደ እርሱ መልሰው። የሚጠላህ ሰው አህያ፣ ጭነት ከብዶት ወድቆ ብታየው ርዳው እንጂ ትተኸው አትሂድ። “በዳኝነት ጊዜ በድኻው ላይ ፍርድ አታጓድልበት። ከሐሰት ክስ ራቅ፤ በደል የሌለበትን ወይም ጻድቁን ሰው ለሞት አሳልፈህ አትስጥ፣ በደለኛውን ንጹሕ አላደርግምና። “ጕቦ አትቀበል፤ ጕቦ አጥርተው የሚያዩትን ሰዎች ዐይን ያሳውራል፤ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና። “መጻተኛውን አትጨቍን፤ በግብጽ መጻተኛ ስለ ነበራችሁ፣ መጻተኛ ምን እንደሚሰማው እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁና። “ስድስት ዓመት በዕርሻህ ላይ ዝራ፤ አዝመራንም ሰብስብ፤ ነገር ግን በሰባተኛው ዓመት ምድሪቱን ሳትጠቀምባትና ሳታርሳት እንዲሁ ተዋት፤ ከዚያም በወገንህ መካከል ያሉት ድኾች ከርሷ ምግብ ያገኛሉ፤ የዱር አራዊትም ከእነርሱ የተረፈውን ይበላሉ። በወይን ቦታህና በወይራ ዛፎችህም ላይ እንዲሁ አድርግ። “ስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፤ በሬህና አህያህ በቤትህ የተወለደው ባሪያና መጻተኛው ያርፉ ዘንድ በሰባተኛው ቀን ምንም አትሥራ። “ያልኋችሁን ሁሉ ታደርጉ ዘንድ ተጠንቀቁ፤ የሌሎችን አማልክት ስም አትጥሩ፤ ከአፋችሁም አይስሙ።

