ዘፀአት 16:9-21

ዘፀአት 16:9-21 NASV

ከዚያም ሙሴ አሮንን፣ “ ‘ማጕረምረማችሁን እርሱ ሰምቷልና ወደ እግዚአብሔር ፊት ቅረቡ’ ብለህ ለመላው የእስራኤል ማኅበር ተናገር” አለው። አሮንም ለመላው የእስራኤል ማኅበር ሲናገር ሳለ ወደ ምድረ በዳው ተመለከቱ፤ በዚያም የእግዚአብሔር ክብር በደመናው ላይ ተገልጦ ይታይ ነበር። እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “የእስራኤላውያንን ማጕረምረም ሰምቻለሁ፤ ይህን ንገራቸው፤ ‘ፀሓይ ከመጥለቋ በፊት ሥጋ ትበላላችሁ፤ ሲነጋም እንጀራ ትበላላችሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ መሆኔን ታውቃላችሁ።’ ” በዚያች ምሽት ድርጭቶች መጥተው ሰፈሩን አለበሱት፤ በነጋውም በሰፈሩ ዙሪያ ጤዛ ተኝቶበት ነበር። ጤዛው ከረገፈ በኋላ በሜዳው ላይ ስስ የሆነ ዐመዳይ የሚመስል የተጋገረ ነገር በምድረ በዳው ላይ ታየ። እስራኤላውያንም ይህን ባዩ ጊዜ ምን እንደ ሆነ ባለማወቃቸው እርስ በርሳቸው፣ “ይህ ነገር ምንድን ነው?” ተባባሉ። ሙሴም፣ “ይህ ትበሉት ዘንድ እግዚአብሔር የሰጣችሁ እንጀራ ነው አላቸው። እግዚአብሔር ያዘዘው ይህ ነው፤ ‘እያንዳንዱ የሚያስፈልገውን ያህል ይሰብስብ፤ በድንኳናችሁ ባለው ሰው ልክ ለእያንዳንዱ አንድ ጎሞር ውሰዱ’ ” ብሎ እግዚአብሔር አዝዟል። እስራኤላውያንም እንደ ተነገራቸው አደረጉ፤ አንዳንዶች አብዝተው፣ አንዳንዶች ደግሞ አሳንሰው ሰበሰቡ። የሰበሰቡትን በጎሞር በሰፈሩ ጊዜ፣ ብዙ የሰበሰበ አላተረፈም፤ ጥቂትም የሰበሰበ አልጐደለበትም፤ እያንዳንዱ የሰበሰበው የሚያስፈልገውን ያህል ሆነ። ሙሴም፣ “ማንም ከዚህ ለነገ ምንም ማስተረፍ የለበትም” አላቸው። ሆኖም ግን አንዳንዶቹ ሙሴ የተናገረውን ቸል በማለት ከሰበሰቡት ውስጥ ከፊሉን አስተርፈው አሳደሩ፤ በማግስቱም ጧት ተልቶ መሽተት ጀመረ፤ ስለዚህ ሙሴ ተቈጣቸው። በየማለዳው እያንዳንዱ የሚያስፈልገውን ያህል ሰበሰበ፤ ፀሓዩ እየበረታ በሄደም ጊዜ ቀለጠ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}