ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ “እስራኤላውያን ተመልሰው በሚግዶልና በባሕሩ መካከል ባለው በፊሀሒሮት አጠገብ እንዲሰፍሩ ንገራቸው፤ በበኣልዛፎንም አንጻር በባሕሩ አጠገብ ይስፈሩ። ‘ፈርዖን እስራኤላውያን ግራ ተጋብተው በምድረ በዳ በመቅበዝበዝ ይንከራተታሉ’ ብሎ ያስባል። እኔም የፈርዖንን ልብ ስለማደነድነው ያሳድዳቸዋል፤ ነገር ግን በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ ለራሴ ክብርን አገኛለሁ፤ ግብጻውያንም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ።” እስራኤላውያንም ይህንኑ አደረጉ። የግብጽ ንጉሥ ሕዝቡ መሄዳቸው በተነገረው ጊዜ፣ ፈርዖንና ሹማምቱ ስለ እነርሱ የነበራቸውን ሐሳብ በመለወጥ፣ “ምን ማድረጋችን ነው? እስራኤላውያን እንዲሄዱ ለቀቅናቸው፤ አገልግሎታቸውንም ዐጣን” አሉ። ስለዚህ ሠረገላው እንዲዘጋጅለት አደረገ፤ ሰራዊቱንም ይዞ ተንቀሳቀሰ። ስድስት መቶ ምርጥ ሠረገላዎችን ከሌሎች የግብጽ ሠረገላዎች ጋራ ከነጦር አዛዦቻቸው አሰልፎ ተነሣ። እግዚአብሔር የንጉሡን የፈርዖንን ልብ ስለ አደነደነው በልበ ሙሉነት ከግብጽ የሚወጡትን እስራኤላውያን አሳደዳቸው። ግብጻውያን፣ ይኸውም የፈርዖን ፈረሶችና ሠረገላዎች፣ ፈረሰኞችና እግረኞች ሁሉ እስራኤላውያንን አሳደዷቸው፤ በበኣልዛፎን አንጻር በባሕሩ አጠገብ በፊሀሒሮት ሰፍረው ሳሉ ደረሱባቸው። ፈርዖን በቀረበ ጊዜ እስራኤላውያን ቀና ብለው ተመለከቱ፤ እነሆ፣ ግብጻውያን ይከታተሏቸው ነበር፤ እነርሱም በታላቅ ፍርሀት ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። እነርሱም ሙሴን እንዲህ አሉት፤ “በምድረ በዳ እንድንሞት ያመጣኸን በግብጽ መቃብር ቦታ ጠፍቶ ነውን? ከግብጽ አውጥተህ ምን አደረግህልን? በግብጽ ሳለን፣ ‘ተወን እባክህ፤ ግብጻውያንን እናገልግል’ አላልንህም ነበርን? በምድረ በዳ ከምንሞት ግብጻውያንን ብናገለግል ይሻል ነበር!” ሙሴም ለሕዝቡ መለሰላቸው፤ “አትሸበሩ፣ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር ዛሬ የሚያደርግላችሁን መታደግ ታያላችሁ፤ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብጻውያንን ዳግም አታዩአቸውም። እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፤ እናንተ ያለባችሁ መታገሥ ብቻ ነው።” ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ለምን ትጮኹብኛላችሁ? ይልቅስ እስራኤላውያንን ወደ ፊት እንዲጓዙ ንገራቸው፤ ውሃውን ለመክፈል በትርህን አንሣና እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ፤ እስራኤላውያን በባሕሩ ውስጥ በየብስ ይሻገራሉ። ተከትለዋቸው እንዲገቡም የግብጻውያንን ልብ አጸናለሁ፤ በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ፣ በሠረገሎቹና በፈረሰኞቹ ለራሴ ክብርን አገኛለሁ። በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ በከበርሁ ጊዜ፣ ግብጻውያን እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” ከዚያም ከእስራኤል ሰራዊት ፊት ፊት ሆኖ ሲሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ተመለሰና ወደ ኋላቸው መጣ፤ የደመናውም ዐምድ እንዲሁ ከፊት ተነሥቶ ከኋላቸው ቆመ፤ በግብጽና በእስራኤል ሰራዊት መካከል በመሆን፣ ሌሊቱን ሙሉ ደመናው በአንድ በኩል ጨለማን ሲያመጣ፣ በሌላው በኩል ብርሃን አመጣ፤ ስለዚህ ሌሊቱን በሙሉ አንዱ ወደ ሌላው ሊጠጋ አልቻለም። ሙሴ እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ እግዚአብሔር ሌሊቱን በሙሉ ብርቱ የምሥራቅ ነፋስ አስነሥቶ ባሕሩን ወደ ኋላ በማሸሽ ደረቅ ምድር አደረገው፤ ውሃውም ተከፈለ። እስራኤላውያን ውሃው በግራና በቀኝ እንደ ግድግዳ ሆኖ በየብስ በባሕሩ ውስጥ ዐለፉ። ግብጻውያንም አሳደዷቸው፤ የፈርዖን ፈረሶች፣ ሠረገሎችና ፈረሰኞች በሙሉ ተከትለዋቸው ወደ ባሕሩ ገቡ። ሲነጋጋም እግዚአብሔር በእሳትና በደመና ዐምድ ሆኖ የግብጻውያንን ሰራዊት ቍልቍል ተመለከተ፤ በግብጻውያን ሰራዊት ላይም ሽብር ላከባቸው። መንዳት እንዳይችሉም የሠረገላዎቹን መሽከርከሪያዎች አቈላለፈባቸው፤ ግብጻውያኑም፣ “ከእስራኤላውያን እንሽሽ! እግዚአብሔር ግብጽን እየተዋጋላቸው ነው” አሉ። ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “ውሃው ግብጻውያንን ሠረገሎቻቸውንና ፈረሰኞቻቸውን ተመልሶ እንዲሸፍናቸው እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ” አለው። ሙሴም እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ ንጋት ላይም ባሕሩ ወደ ቀድሞ ቦታው ተመለሰ። ግብጻውያን ከውሃው ሸሹ፤ እግዚአብሔርም ግብጻውያንን በባሕሩ ውስጥ ጣላቸው። ውሃውም ተመልሶ እስራኤላውያንን ተከትለው ወደ ባሕሩ የገቡትን ሠረገሎች፣ ፈረሰኞች፣ መላውን የፈርዖን ሰራዊት ሁሉ ሸፈነ። አንድም እንኳ አልተረፈም። እስራኤላውያን ግን ውሃው ግራና ቀኝ እንደ ግድግዳ ሆኖ፣ በደረቅ ምድር ባሕሩን ተሻገሩ። በዚያች ዕለት እግዚአብሔር እስራኤልን ከግብጻውያን እጅ አዳናቸው፤ እስራኤልም የግብጻውያን ሬሳ በባሕሩ ዳርቻ ወድቆ ተመለከቱ። እስራኤላውያን እግዚአብሔር በግብጻውያን ላይ ያደረገውን ታላቅ ኀይል ባዩ ጊዜ፣ እግዚአብሔርን ፈሩ፤ በእግዚአብሔርና በባሪያው በሙሴም አመኑ።
ዘፀአት 14 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፀአት 14
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፀአት 14:1-31
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች