ዘፀአት 10:21-29

ዘፀአት 10:21-29 NASV

ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “በግብጽ ላይ ድቅድቅ ጨለማ እንዲወርድ እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ” አለው። ሙሴም እጁን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ በመላው ግብጽ ላይ ለሦስት ቀናት ድቅድቅ ያለ ጨለማ ሆነ። በእነዚያ ሦስት ቀናት ውስጥ አንዱ ሌላውን ማየት ወይም ከነበረበት ቦታ መንቀሳቀስ አይችልም ነበር። ይሁን እንጂ እስራኤላውያን በሚኖሩበት ስፍራ ሁሉ ብርሃን ነበር። ከዚያም ፈርዖን ሙሴን አስጠርቶ፣ “ሄዳችሁ እግዚአብሔርን አምልኩ፤ ሴቶቻችሁና ልጆቻችሁ ሳይቀሩ ዐብረዋችሁ ይሂዱ፤ በጎቻችሁ፣ ፍየሎቻችሁና የጋማ ከብቶቻችሁ ብቻ እዚሁ ይቅሩ” አለው። ሙሴም እንዲህ አለው፤ “ለአምላካችን ለእግዚአብሔር መሥዋዕትና የሚቃጠል መሥዋዕት እንድንሠዋ ፍቀድልን፤ እንስሶቻችን ሁሉ ዐብረው መሄድ አለባቸው። አንድ ሰኰና እንኳ አይቀርም። ከእንስሶቻችን መካከል ለአምላካችን ለእግዚአብሔር አምልኮ የምናቀርባቸው ይኖራሉ፤ ሆኖም እዚያ ከመድረሳችን በፊት እግዚአብሔርን ለማምለክ የምናቀርባቸው እንስሳት የትኞቹ እንደ ሆኑ አስቀድመን ለይተን ማወቅ አንችልም።” ነገር ግን እግዚአብሔር የፈርዖንን ልብ አደነደነ፤ ፈርዖንም ሕዝቡን መልቀቅ አልፈቀደም። ፈርዖን ሙሴን፣ “ከፊቴ ጥፋ! ሁለተኛ እኔ ዘንድ እንዳትደርስ! ፊቴን ባየህበት በዚያ ቀን ፈጽመህ እንደምትሞት ዕወቅ” አለው። ሙሴም፣ “እንዳልከው ይሁን፤ እኔም ዳግመኛ ከፊትህ አልደርስም” አለው።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}