አስቴር 8:1-8

አስቴር 8:1-8 NASV

በዚያ ዕለት ንጉሥ ጠረክሲስ የአይሁድን ጠላት የሐማን ቤት ንብረት ለንግሥት አስቴር ሰጣት፤ አስቴርም መርዶክዮስ እንዴት እንደሚዛመዳት ለንጉሡ ነግራው ስለ ነበር፣ መርዶክዮስ ወደ ንጉሡ ዘንድ ቀረበ። ንጉሡ ከሐማ መልሶ የወሰደውን ባለማኅተም ቀለበት አውልቆ ለመርዶክዮስ ሰጠው፤ አስቴርም መርዶክዮስን በሐማ ቤት ንብረት ላይ ሾመችው። አስቴር በንጉሡ እግር ላይ ወድቃ በማልቀስ ልመናዋን እንደ ገና አቀረበች። አጋጋዊው ሐማ በአይሁድ ላይ የሸረበው ክፉ ሤራ እንዲሽር ለመነችው። ከዚያም ንጉሡ የወርቅ ዘንጉን ለአስቴር ዘረጋላት፤ እርሷም ተነሥታ በፊቱ ቆመች። እንዲህም አለች፤ “ንጉሡን ደስ የሚያሠኘውና እኔም በፊቱ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ፣ ጕዳዩም በንጉሡ ዘንድ ተገቢ ሆኖ ከተገኘና በእኔም ደስ ከተሠኘ፣ የአጋጋዊው የሐመዳቱ ልጅ ሐማ በንጉሡ አውራጃዎች ሁሉ የሚገኙትን አይሁድ ለማጥፋት የሸረበውን ሤራና የጻፈውን ደብዳቤ የሚሽር ትእዛዝ ይጻፍ። በሕዝቤ ላይ መዓት ሲወርድ እያየሁ እንዴት ልታገሥ እችላለሁ? የዘመዶቼንስ መጥፋት እያየሁ እንዴት መቋቋም እችላለሁ?” ንጉሥ ጠረክሲስም ለንግሥት አስቴርና ለአይሁዳዊው ለመርዶክዮስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እነሆ ሐማ አይሁድን ለማጥፋት ስላቀደ፣ ቤት ንብረቱን ለአስቴር ሰጥቻለሁ፤ እርሱንም በዕንጨት ላይ ሰቅለውታል። በንጉሥ ስም የተጻፈና በቀለበቱ የታተመ ደብዳቤ ሊሻር ስለማይችል፣ እናንተ ደግሞ አይሁድን በተመለከተ መልካም መስሎ የታያችሁን ሌላ ዐዋጅ በንጉሡ ስም ጽፋችሁ በንጉሡ የቀለበት ማኅተም ዐትሙት።”