አስቴር 5:9-14

አስቴር 5:9-14 NASV

ሐማ በዚያ ቀን ደስ ብሎትና መንፈሱ ረክቶ ወጣ፤ ነገር ግን መርዶክዮስን በንጉሡ በር ላይ ሲያየው ከተቀመጠበት አለመነሣቱንና በፊቱም አለመንቀጥቀጡን ሲመለከት፣ ቍጣው በመርዶክዮስ ላይ ነደደ። ሐማ ግን እንደ ምንም ራሱን ተቈጣጥሮ ወደ ቤቱ ሄደ። ወዳጆቹንና ሚስቱን ዞሳራን አስጠርቶ በአንድነት ከሰበሰባቸው በኋላ፣ ሐማ ስለ ሀብቱ ታላቅነት፣ ስለ ልጆቹ ብዛት እንዲሁም ንጉሡ የቱን ያህል እንዳከበረው፣ ከሌሎቹም መኳንንትና ሹማምት ይበልጥ እንዴት ከፍ ከፍ እንዳደረገው እያጋነነ ነገራቸው። ሐማም፣ “ምን ይህ ብቻ” አለ፤ “ንግሥት አስቴር ባዘጋጀችው ግብዣ ላይ ከንጉሡ ጋራ እንድገኝ የጋበዘችው ሰው አንድ እኔ ብቻ ነኝ፤ ነገም ከንጉሡ ጋራ ጋብዛኛለች። ነገር ግን አይሁዳዊው መርዶክዮስ በንጉሡ በር ላይ ተቀምጦ ካየሁት ይህ ሁሉ እኔን ደስ አያሠኘኝም።” ሚስቱ ዞሳራና ወዳጆቹ በሙሉ፣ “ቁመቱ ዐምሳ ክንድ የሆነ መስቀያ አስተክልና መርዶክዮስ እንዲሰቀልበት በጧት ለንጉሡ ንገረው፤ ከዚያም ደስ ብሎህ ከንጉሡ ጋራ ወደ ግብዣው ግባ” አሉት። ይህም ሐሳብ ሐማን እጅግ ደስ አሠኘው፤ መስቀያውንም አስተከለ።