አስቴር 2:1-10

አስቴር 2:1-10 NASV

ከዚህ በኋላ ንጉሡ ጠረክሲስ ቍጣው ሲበርድለት አስጢንን፣ ያደረገችውን ነገርና በርሷም ላይ ያስተላለፈውን ዐዋጅ ዐሰበ። ከዚያም የንጉሡ የቅርብ አገልጋዮች እንዲህ የሚል ሐሳብ አቀረቡ፤ “ለንጉሡ ቈንጆ ልጃገረዶች ይፈለጉለት፤ እነዚህን ሁሉ ቈንጆ ልጃገረዶች በሱሳ ግንብ ወደሚገኘው ልዩ የሴቶች መኖሪያ ቦታ እንዲያመጡ፣ ንጉሡ በግዛቱ በሚገኙት አውራጃዎቹ ሁሉ ባለሥልጣኖችን ይሹም፤ እነርሱም የሴቶች የበላይ ኀላፊ በሆነው በንጉሡ ጃንደረባ በሄጌ ኀላፊነት ሥር ይሁኑ፤ የውበትም እንክብካቤ ይደረግላቸው። ከዚያም ንጉሡን ደስ የምታሠኘው ልጃገረድ በአስጢን ፈንታ ንግሥት ትሁን።” ምክሩ ንጉሡን ደስ አሠኘው፤ በተባለውም መሠረት አደረገ። በዚህ ጊዜ ከብንያም ነገድ የቂስ ልጅ፣ የሰሜኢ ልጅ፣ የኢያዕር ልጅ መርዶክዮስ የሚባል አንድ አይሁዳዊ በሱሳ ግንብ ይኖር ነበር፤ እርሱም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከማረካቸው ከይሁዳ ንጉሥ ከኢኮንያን ጋራ ከኢየሩሳሌም በምርኮ ከተወሰዱት አንዱ ነበር። መርዶክዮስ አንዲት ሀደሳ የምትባል የአጎቱ ልጅ ነበረችው፤ አባትና እናት ስላልነበራት ያሳደጋት እርሱ ነበር። አስቴር ተብላ የምትጠራው ይህች ልጃገረድ በተክለ ሰውነቷም ሆነ በመልኳ እጅግ ውብ ነበረች። አባቷና እናቷ ከሞቱ በኋላ መርዶክዮስ እንደ ራሱ ልጅ አድርጎ ወሰዳት። የንጉሡ ትእዛዝና ዐዋጅ በወጣ ጊዜ፣ ብዙ ልጃገረዶች ወደ ሱሳ ግንብ ተወስደው ለጠባቂው ለሄጌ ተሰጡ፤ አስቴርም ወደ ንጉሡ ቤተ መንግሥት ተወስዳ፣ ለሴቶቹ ጠባቂ ለሄጌ በዐደራ ተሰጠች። ልጃገረዲቱም ደስ አሠኘችው፤ በርሱም ዘንድ መወደድን አተረፈች፤ እርሱም የውበት መከባከቢያዋንና የተለየ ምግብ ወዲያውኑ ሰጣት። ከቤተ መንግሥቱ የተመረጡ ሰባት ደንገጡሮችን በመመደብም እርሷንና ደንገጡሮቿን ምርጥ ወደ ሆነው የሴቶች መጠበቂያ አዛወረ። መርዶክዮስ እንዳትናገር አዝዟት ስለ ነበር፣ አስቴር የየት አገር ሰውና የእነማን ወገን እንደ ሆነች አልገለጸችም።