ኤፌሶን 6:1-9
ኤፌሶን 6:1-9 NASV
ልጆች ሆይ፤ በጌታ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ፤ ይህ ተገቢ ነውና። “አባትህንና እናትህን አክብር” በሚለው ቀዳሚ ትእዛዝ ውስጥ ያለው ተስፋ፣ “መልካም እንዲሆንልህ፣ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም” የሚል ነው። አባቶች ሆይ፤ እናንተም ልጆቻችሁን አታስቈጧቸው፤ ነገር ግን በጌታ ምክርና ተግሣጽ አሳድጓቸው። ባሮች ሆይ፤ ለክርስቶስ እንደምትታዘዙ፣ በምድር ጌቶቻችሁ ለሆኑት በአክብሮትና በፍርሀት፣ በቅን ልብም ታዘዙ፤ ለታይታና ከእነርሱ ሙገሳን ለማግኘት ሳይሆን፣ እንደ ክርስቶስ ባሮች የእግዚአብሔርን ፈቃድ ከልብ በመፈጸም ታዘዟቸው። ሰውን ሳይሆን ጌታን እንደምታገለግሉ ሆናችሁ በሙሉ ልብ አገልግሉ፤ ምክንያቱም ባሪያም ሆነ ነጻ ሰው ለሚያደርገው በጎ ነገር ሁሉ ሽልማቱን ከጌታ እንደሚቀበል ታውቃላችሁ። እናንተም ጌቶች ሆይ፤ ለባሮቻችሁ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ የእነርሱም፣ የእናንተም ጌታ የሆነው በሰማይ እንዳለ፣ የሰውንም ፊት አይቶ እንደማያደላ ታውቃላችሁና አታስፈራሯቸው።


