ኤፌሶን 6:1-9 - Compare All Versions
ኤፌሶን 6:1-9 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
ልጆች ሆይ፤ በጌታ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ፤ ይህ ተገቢ ነውና። “አባትህንና እናትህን አክብር” በሚለው ቀዳሚ ትእዛዝ ውስጥ ያለው ተስፋ፣ “መልካም እንዲሆንልህ፣ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም” የሚል ነው። አባቶች ሆይ፤ እናንተም ልጆቻችሁን አታስቈጧቸው፤ ነገር ግን በጌታ ምክርና ተግሣጽ አሳድጓቸው። ባሮች ሆይ፤ ለክርስቶስ እንደምትታዘዙ፣ በምድር ጌቶቻችሁ ለሆኑት በአክብሮትና በፍርሀት፣ በቅን ልብም ታዘዙ፤ ለታይታና ከእነርሱ ሙገሳን ለማግኘት ሳይሆን፣ እንደ ክርስቶስ ባሮች የእግዚአብሔርን ፈቃድ ከልብ በመፈጸም ታዘዟቸው። ሰውን ሳይሆን ጌታን እንደምታገለግሉ ሆናችሁ በሙሉ ልብ አገልግሉ፤ ምክንያቱም ባሪያም ሆነ ነጻ ሰው ለሚያደርገው በጎ ነገር ሁሉ ሽልማቱን ከጌታ እንደሚቀበል ታውቃላችሁ። እናንተም ጌቶች ሆይ፤ ለባሮቻችሁ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ የእነርሱም፣ የእናንተም ጌታ የሆነው በሰማይ እንዳለ፣ የሰውንም ፊት አይቶ እንደማያደላ ታውቃላችሁና አታስፈራሯቸው።
ኤፌሶን 6:1-9 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
ልጆች ሆይ! ተገቢ ነገር ስለ ሆነ በጌታ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ። “አባትህንና እናትህን አክብር” የሚለው ትእዛዝ የተስፋ ቃል ያለበት የመጀመሪያ ትእዛዝ ነው፤ ይህንንም ብታደርግ “ሁሉ ነገር ይሰምርልሃል፤ በዚህም ምድር ላይ ዕድሜህ ይረዝማል።” እናንተም ወላጆች ሆይ! በጌታ በኢየሱስ ሥነ ሥርዓትን በማስተማር፥ በማረምና በመገሠጽ አሳድጉአቸው እንጂ ልጆቻችሁን በማስቈጣት አታስመርሩአቸው። እናንተ አገልጋዮች ሆይ! በሥጋ ጌቶቻችሁ ለሆኑት በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ ታዘዙ፤ ለክርስቶስ በምታገለግሉት ዐይነት በልብ ቅንነት ታዘዙአቸው። የምትታዘዙትም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ከልብ እንደሚፈጽሙ እንደ ክርስቶስ አገልጋዮች ሆናችሁ ነው እንጂ ሰውን ደስ ለማሰኘት ብላችሁ ለታይታ አይሁን። ሰውን ሳይሆን ጌታን እንደምታገለግሉ አድርጋችሁ በመልካም ፈቃድ አገልግሉ። ባሪያም ሆነ ጌታ እያንዳንዱ በሠራው መልካም ሥራ ከጌታ ዋጋውን የሚቀበል መሆኑን ታውቃላችሁ። እናንተም ጌቶች ሆይ! ለሰው ፊት የማያዳላ የእናንተና የእነርሱ ጌታ በሰማይ እንዳለ በማስታወስ ዛቻችሁን ትታችሁ ለአገልጋዮቻችሁ መልካም አድርጉላቸው።
ኤፌሶን 6:1-9 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
ልጆች ሆይ፥ ለወላጆቻችሁ በጌታችን ታዘዙ፤ ይህ የሚገባ ነውና። በሕግም ተስፋ ያለው የመጀመሪያው ትእዛዝ ይህ ነው፥ “አባትህንና እናትህን አክብር፤ መልካም ይሆንልህ ዘንድ፥ በምድር ላይም ዕድሜህ ይረዝም ዘንድ።” እናንተም አባቶች ሆይ፥ ልጆቻችሁን በእግዚአብሔር ተግሣጽና ምክር አሳድጉአቸው እንጂ አታስቈጡአቸው። አገልጋዮችም በሥጋችሁ ለሚገዙአችሁ ጌቶቻችሁ በፍርሀትና በመደንገጥ፥ በሰፊ ልብም ለክርስቶስ እንደምትገዙ ታዘዙ። የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባሮች እንጂ ለሰው ደስ እንደሚያሰኝ ለታይታ አይደለም። ለሰው ሳይሆን ለእግዚአብሔር እንደምትገዙ በፍጹም ሰውነታችሁ በፍቅርና በበጎ ፈቃድ ተገዙላቸው። ጌታም ቢሆን፥ አገልጋይም ቢሆን መልካም ያደረገ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ እንደሚያገኝ ታውቃላችሁና። እናንተም ጌቶች ሆይ፥ ቍጣችሁን እያበረዳችሁ፥ በደላቸውንም ይቅር እያላችሁ፥ ትክክለኛውን አድርጉላቸው፤ ፊት አይቶ የማያዳላ ጌታ በእነርሱና በእናንተ ላይ በሰማይ እንደ አለ ታውቃላችሁና።
ኤፌሶን 6:1-9 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))
ልጆች ሆይ፥ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፥ ይህ የሚገባ ነውና። መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር፤ እርስዋም የተስፋ ቃል ያላት ፊተኛይቱ ትእዛዝ ናት። እናንተም አባቶች ሆይ፥ ልጆቻችሁን በጌታኣ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው። ባሪያዎች ሆይ፥ ለክርስቶስ እንደምትታዘዙ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ በልባችሁ ቅንነት በሥጋ ጌቶቻችሁ ለሆኑ ታዘዙ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች እንጂ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ አትሁኑ። ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምትገዙ በትጋትና በበጎ ፈቃድ ተገዙ፤ ባሪያ ቢሆን ወይም ጨዋ ሰው፥ እያንዳንዱ የሚያደርገውን መልካም ነገር ሁሉ ከጌታ በብድራት እንዲቀበለው ታውቃላችሁና። እናንተም ጌቶች ሆይ፥ ዛቻውን ትታችሁ እንዲሁ አድርጉላቸው፥ በእነርሱና በእናንተ ላይ የሚገዛው ጌታ በሰማይ እንዳለ ለሰው ፊትም እንዳያደላ ታውቃላችሁና።
ኤፌሶን 6:1-9 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))
ልጆች ሆይ! ተገቢ ነውና ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ። “አባትህንና እናትህን አክብር፤” ከተስፋ ቃል ጋር የተሰጠ የመጀመሪያው ትእዛዝ ነው፤ “መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም” እናንተም አባቶች ሆይ! ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቈጡአቸው። አገልጋዮች ሆይ! ለክርስቶስ እንደምትታዘዙ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ፥ በልባችሁ ቅንነት በምድር ጌቶቻችሁ ለሆኑ ታዘዙ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባርያዎች እንጂ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ አትሁኑ። ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታገለግሉ በጽኑ ፍላጎት ተገዙ፤ ባርያም ሆነ ነጻ ሰው፥ እያንዳንዱ ለሚያደርገው መልካም ነገር ሁሉ ከጌታ ብድራቱን እንደሚቀበል ታውቃላችሁ። እናንተም ጌቶች ሆይ! ዛቻውን ትታችሁ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ በእነርሱና በእናንተ ላይ የሚገዛው ጌታ በሰማይ እንዳለ ለሰው ፊትም እንደማያዳላ ታውቃላችሁ።