መክብብ 2:1-11

መክብብ 2:1-11 NASV

እኔም በልቤ፣ “መልካም የሆነውን ለማወቅ፣ በተድላ እፈትንሃለሁ” አልሁ፤ ነገር ግን ያም ከንቱ ነበረ። ደግሞም፣ “ሣቅ ሞኝነት ነው፤ ተድላስ ምን ይጠቅማል?” አልሁ። አሁንም አእምሮዬ በጥበብ እየመራኝ ራሴን በወይን ጠጅ ደስ ለማሠኘት፣ ሞኝነትንም ለመያዝ ሞከርሁ፤ ሰዎች በዐጭር የሕይወት ዘመናቸው ከሰማይ በታች ባለው ላይ ቢሠሩት ሊጠቅማቸው የሚችል ምን እንደ ሆነ ለማየት ፈለግሁ። ታላላቅ ነገሮችን አከናወንሁ፤ ለራሴ ቤቶችን ሠራሁ፤ ወይንንም ተከልሁ፤ አትክልትን ተከልሁ፤ የመዝናኛ ስፍራዎችን አዘጋጀሁ፤ በእነዚህም ላይ ፍሬ የሚያፈሩ የዛፍ ዐይነቶችን ሁሉ ተከልሁባቸው፤ የሚለመልሙ ዛፎችን፣ ለቦይ የሚሆኑ የውሃ ማጠራቀሚያዎችን ሠራሁ። ወንድና ሴት ባሪያዎችን ገዛሁ፤ በቤቴም የተወለዱ ሌሎች ባሪያዎች ነበሩኝ። ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከነበሩት ይልቅ ብዙ የከብት፣ የበግና የፍየል መንጋዎች ነበሩኝ። ለራሴም ብርንና ወርቅን፣ የነገሥታትና የአውራጃዎችን ሀብት አካበትሁ፤ ወንድና ሴት አዝማሪዎች፣ የሰው መደሰቻ የሆኑ ቅምጦች ነበሩኝ። ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ እጅግ ታላቅ ሆንሁ፤ በዚህ ሁሉ ጥበቤ ከእኔ ጋራ ነበረች። ዐይኔ የፈለገውን ሁሉ አልከለከልሁትም፤ ለልቤም ምድራዊ ደስታን አልነፈግሁትም፤ ልቤ በሠራሁት ሁሉ ደስ አለው፤ ይህም የድካሜ ሁሉ ዋጋ ነበረ። ሆኖም እጆቼ የሠሩትን ሁሉ፣ ለማግኘትም የደከምሁትን ድካም ሁሉ ሳስብ፣ ሁሉም ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነበር፤ ከፀሓይ በታች ምንም ትርፍ አልነበረም።