ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዞች በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስጠናቸው፤ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣም ስለ እነርሱ ተናገር። በእጅህ ላይ ምልክት አድርገህ እሰራቸው፤ በግንባርህም ላይ ይሁኑ። በቤትህ መቃኖችና በግቢህም በሮች ላይ ጻፋቸው። አምላክህ እግዚአብሔር ለአንተ ለመስጠት ለአባቶችህ ለአብርሃም፣ ለይሥሐቅና ለያዕቆብ ወደ ማለላቸው ምድር ሲያስገባህ፣ በዚያም ያልሠራሃቸውን ታላላቅና ያማሩ ከተሞችን፣ የራስህ ባልነበሩ መልካም ነገሮች ሁሉ የተሞሉ ቤቶችን፣ ያልቈፈርሃቸውን የውሃ ጕድጓዶች፣ ያልተከልሃቸውን የወይን ተክሎችና የወይራ ዛፎች ሲሰጥህና በልተህም ስትጠግብ፣ ከባርነት ምድር ከግብጽ ያወጣህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ! አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ፤ እርሱን ብቻ አገልግል፤ በስሙም ማል። በዙሪያህ ያሉ ሕዝቦች የሚያመልኳቸውን ሌሎች አማልክት አትከተል፤ ምክንያቱም በመካከልህ ያለው አምላክህ እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ ስለ ሆነ፣ በአንተም ላይ ቍጣው ስለሚነድድ፣ ከምድር ገጽ ያጠፋሃል። በማሳህ እንዳደረግኸው እግዚአብሔር አምላክህን አትፈታተነው። አምላካችሁ እግዚአብሔር የሰጣችሁን ትእዛዞች፣ ምስክርነቶችና ሥርዐቶች በጥንቃቄ ጠብቁ። መልካም እንዲሆንልህና እግዚአብሔር ለአባቶችህ በመሐላ እንድትወርሳት፣ በእግዚአብሔር ፊት ተስፋ የሰጣቸውን መልካሚቱን ምድር ገብተህ ቀናና መልካም የሆነውን አድርግ፤ እግዚአብሔር በተናገረው መሠረትም ጠላቶችህን ሁሉ ከፊትህ ታስወጣለህ። በሚመጡት ዘመናት ልጅህ፣ “አምላካችን እግዚአብሔር ያዘዛችሁ የምስክርነቶቹ፣ የሥርዐቶቹና የሕጎቹ ትርጕም ምንድን ነው?” ብሎ በሚጠይቅህ ጊዜ፣ እንዲህ በለው፤ “እኛ በግብጽ የፈርዖን ባሮች ነበርን፤ እግዚአብሔር ግን በብርቱ እጅ ከግብጽ አወጣን። እኛ በዐይናችን እያየን እግዚአብሔር ታላላቅና አስፈሪ የሆኑ ታምራዊ ምልክቶችና ድንቆችን በግብጽ፣ በፈርዖንና በመላው ቤተ ሰዎቹ ላይ አደረገ። እኛን ግን ለአባቶቻችን በመሐላ ተስፋ ወደ ሰጣቸው ምድር ሊያስገባንና ሊሰጠን ከዚያ አወጣን። ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ ምን ጊዜም መልካም እንዲሆንልንና በሕይወት እንድንኖር ይህን ሥርዐት ሁሉ እንድንፈጽም፣ አምላካችንንም እግዚአብሔርን እንድንፈራ እግዚአብሔር አዘዘን። እንግዲህ ይህን ሁሉ ሕግ እርሱ ባዘዘን መሠረት፣ በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት ተጠንቅቀን ከጠበቅን፣ ያ ለእኛ ጽድቃችን ይሆናል።”
ዘዳግም 6 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘዳግም 6
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘዳግም 6:6-25
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች